በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።
መቻል ከሀዲያ ሆሳዕና
የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር የመጀመርያውን ዙር በበላይነት የፈፀሙትን መቻሎችን ዘጠነኛ ሆነው ካጠናቀቁት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ያገናኛል።
በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመሩት መቻሎች ምንም እንኳን በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጥቂት ሳምንታት በውጤት ሆነ በእንቅስቃሴ ወጥ ለመሆን ቢቸገሩም የአንደኛ ዙር አፈፃፀማቸው እጅግ አስደናቂ የሚባል ነው።ይህን ግስጋሴ በማስቀጠል በዓመቱ መጨረሻ በሰንጠረዡ አናት በሚደረገው ፉክክር የሚጠበቁት መቻሎች የሁለተኛ ዙር ፈተናቸውን ነገ አንድ ብለው ይጀምራሉ።
በመጀመሪያው ዙር ካደረጓቸው አስራ ስድስት ጨዋታዎች አስሩን(63%) የሚሆኑትን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የፈፀሙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሁለተኛው ዙር አለመሸነፍን ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ከጠንካራ የመከለካል መዋቅር ባለፈ በማጥቃቱ ረገድ ፍፁም ደካማ አጋማሽ ያሳለፈው ቡድኑ ይህንን ድክመት እንዴት አሻሽሎ ይቀርባል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
ሁለቱም ቡድኖች ምንም እንኳን ገና ቀሪ ጊዜያት ቢኖሩም እስካሁን ለሁለተኛው ዙር ወደ ስብስባቸው የቀላቀሏቸው ተጫዋቾች የሉም።
በመቻል በኩል ቅጣት ላይ የሚገኘው በኃይሉ ግርማ ብቻ የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ሲሆን በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሀድያ አይቮሪኮስታዊው ግብ ጠባቂ ታፔ አልዛየር ወደ ሀገሩ በማምራቱ የማይኖር ሲሆን በአንፃሩ ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስ ከቅጣት የሚመለስ ይሆናል በተያያዘ ዜና አማካዩ ስንታየሁ ዋለጪ ከክለቡ ጋር ስለመለያየቱም ተሰምቷል።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ተገናኝተው መቻል በአምስቱ የበላይነት ሲነሮረው ሆሳዕና አንድ አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። ጦሩ 10፣ ነብሮቹ 7 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
ይህን መርሃግብር በዋና ዳኝነት ዳንኤል ግርማይ ሲመሩት በረዳትነት ደግሞ ለዓለም ዋሲሁን እና እያሱ ካሳሁን ሲመደቡ አራተኛ ዳኛ በመሆን ደግሞ ሙሉቀን ያረጋል በጋራ ጨዋታውን ይመሩታል።
ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ
ምሽት አንድ ሰዓት ሲል ደግሞ ጅማሮውን የሚያደርገው መርሃግብር ደግሞ በአራት ነጥቦች ልዩነት አምሰተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ፋሲሎች አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ያገናኛል።
ፍፁም ጉራማይሌ የሆነ የመጀመርያ ዙር ያሳለፉት ፋሲል ከነማዎች የመጀመሪያ ዙር ጉዟቸው ከግምቶች በተቃራኒ ወጥነት የጎደለውን የነበረ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ይህን ጉዞ በመቀልበስ አሁን ላይ ከሊጉ መሪ ያላቸውን የአስር ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በመጀመሪያው ዙር ረዘም ላሉ ሳምንታት በውጤት አልባ ጉዞ ውስጥ የከረሙት ሀዋሳዎች በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት ግን በተወሰነ መልኩ የመሻሻል ፍንጮችን አሳይተዋል።
ከቡድኑ ጋር መቃቃር ውስጥ ገብተው የነበሩት ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን እና አጥቂው ሙጂብ ቃሲም ከክለቡ ጋር ሲለያዩ በምትኩ ደግሞ የቀድሞው አጥቂያቸው እስራኤል እሸቱ ወደ ቀድሞ ቤቱ መመለስ ችለዋል።
በአንፃሩ በዐፄዎቹ ቤት በሀዋሳ ከተማ ከአስደናቂ የመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ በኃላ በጉዳት እና ባለመግባባት በሀዋሳ የተረሳ ይመስል የነበረው ወንድማገኝ ሀይሉ አሁን ላይ ወደ አሜሪካ ያቀናውን ሱራፌል ዳኛቸውን በመተካት ፋሲል ከነማን ተቀላቅሏል።
ሀዋሳ ከተማዎች በነገው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም።
ሁለቱ ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በ14 ጨዋታዎች ተገናኝተው እኩል አራት አራት ጊዜ ሲሸናነፉ ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ፋሲል 17 ሲያስቆጥር ፣ ሀዋሳ 19 ማስቆጠር ችለዋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሐል ዳኝነት አስቻለው ወርቁ እና ዘሪሁን ኪዳኔ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በበኩሉ ደግሞ አራተኛ በመሆን ተሰይሟል።