በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ዐፄዎቹ ከመመራት ተነስተው ኃይቆቹን 2ለ1 በመርታት ወሳኝ ድል አሳክተዋል።
በምሽቱ መርሐግብር ፋሲል ከነማ እና ሀዋሳ ከተማ ሲገናኙ ዐፄዎቹ በ15ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4ለ2 ሲሸነፉ ከተጠቀሙትን አሰላለፍ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ኢዮብ ማቲያስ በመናፍ ዐዎል ተተክቶ ገብቷል። ኃይቆቹ በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር 1-1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ መድኃኔ ብርሃኔ ፣ ታፈሰ ሰለሞን ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና ቸርነት አውሽ በዳዊት ታደሰ ፣ በአምስት ቢጫ ጨዋታው በሚያልፈው ኢዮብ ዓለማየሁ ፣ መጠነኛ ጉዳት ባጋጠመው ዓሊ ሱሌይማን እና ሲሳይ ጋቾ ምትክ ተተክተው ገብተዋል።
ምሽት 1 ሰዓት ላይ በቅርቡ በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ላጡት የሀዋሳ ከተማ የእግርኳስ የጤና ቡድን አባላት በመዘከር በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ኃይቆቹ 7ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የመጀመሪያ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቸርነት አውሽ በጥሩ ዕይታ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ባስገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ መልሶበታል።
ዐፄዎቹ በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ 12ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ሽመክት ጉግሳ ከጌታነህ ከበደ በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ በጥሩ ብቃት መልሶበታል። ሆኖም ግን ሁለቱም ቡድኖች በሚከተሉት ዝግ ያለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ምክንያት ለረጅም ደቂቃዎች ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም።
መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ፋሲሎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ በመውሰድ እና በቁጥር በመብዛት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ቢደርሱም የሀዋሳን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት መጣስ አልቻሉም። 41ኛው ደቂቃ ላይም ኃይቆቹ በግሩም የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ግብ አስቆጥረዋል። ተባረክ ሄፋሞ ባመቻቸለት ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል የደረሰው ታፈሰ ሰለሞን ኳሱን አስደናቂ በሆነ አጨራረስ የቀድሞ ክለቡ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ሦስት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ዐፄዎቹ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር የሚያስችል ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው አማኑኤል ገብረሚካኤል በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በረከት ሳሙኤልን በግሩም ክህሎት አታልሎ በማለፍ ከማቀበል አማራጭ ጋር ባገኘው ክፍት ቦታ ያደረገውን ሙከራ መድኃኔ ብርሃኔ በግሩም ፍጥነት አግዶበታል።
ከዕረፍት መልስ አምሳሉ ጥላሁን እና ይሁን እንዳሻውን አስወጥተው አቤል እንዳለ እና ቃልኪዳን ዘላለምን በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ማጠናከር የቻሉት ፋሲል ከነማዎች 51ኛው ደቂቃ ላይ ቅያሪያቸው ፍሬ ሊያፈራ እጅግ ተቃርቦ ቃልኪዳን ዘላለም ለመምታት በጥሩ ሁኔታ ባመቻቸው ኳስ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ሀዋሳዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መከላከልን ሲመርጡ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን በማጥቃቱ እንቅስቃሴ የበላይነቱን የወሰዱት ፋሲሎች በተደጋጋሚ ወደ ግብ ሲታትሩ 67ኛው ደቂቃ ላይ በዮናታን ፍስሃ አማካኝነት ከረጅም ርቀት ሙከራ ሲያደርጉ በአንድ ደቂቃ ልዩነትም የአጋማሹን የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረዋል። በዚህም አማኑኤል ገብረሚካኤል ከኤልያስ ማሞ በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ሲያስወጣበት በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ጌታነህ ከበደ በግራ እግሩ መሬት ለመሬት ሙከራ ቢያደርግም በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞበታል።
ጨዋታው 76ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በሙሉ ኃይላቸው ሲያጠቁ የነበሩት ፋሲሎች ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ከጥቂት የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ንክኪዎች በኋላ ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል ግብ አድርጎታል። በሁለተኛው አጋማሽ በመከላከል ሥራ ተጠምደው ያሳለፉት ኃይቆቹ በአንጻሩ 81ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ባሻገረው ኳስ በረከት ሳሙኤል በጭንቅላት በመግጨት ያደረገው ሙከራቸው የተሻለው ነበር።
ከዕረፍት መልስ የተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገው ሰፊ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ፋሲሎች 88ኛው ደቂቃ ላይ ከመመራት ተነስተው መሪ የሆኑበትን ግብ ሲያገኙ ጌታነህ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ቃልኪዳን ዘላለም በግሩም ሁኔታ የመታው ኳስ በጸጋአብ ዮሐንስ ተጨርፎ መረቡ ላይ አርፏል። በቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር ተደርጎበት ጨዋታው በፋሲል ከነማ የ2ለ1 ድል አድራጊት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ግብ እስኪቆጠርባቸው ታክቲካሊ ጥሩ እንደነበሩ ነገር ግን የአቋቋም ስህተት ዋጋ እንዳስከፈላቸው ሲናገሩ ሁለተኛውን ግብ ባላሰቡት ሰዓት ማስተናገዳቸው እንቅስቃሴያቸውን እንዳፈረሰባቸው ጠቁመዋል። የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በሚፈልጉት መንገድ እንደተጫወቱ ጠቁመው እንቅስቃሴያቸው በቂ እንደነበር እና ከዕረፍት መልስ ያደረጉት ለውጥ ውጤት እንዲያሳኩ እንዳገዛቸው እና ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ጥሩ እንደነበሩ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።