በሁለተኛው ዙር ቀዳሚ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን የሚካሄዱት ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል
ወልቂጤ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሰራተኞቹ ከወራጅ ለመውጣት ፈረሰኞቹ ደግሞ ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ለመጠጋት የሚያደርጉት ጨዋታ የነገ ቀዳሚው ፍልሚያ ነው።
የመጀመርያውን ዙር በአስር ነጥቦች 14ኛ ደረጃነት ይዘው ያጠናቀቁት ወልቂጤ ከተማዎች ድል ከቀናቸው ስምንት ሳምንታት ተቆጥረዋል። ቡድኑ በተጠቀሱት ሳምንታት ስድስት ሽንፈት ሁለት የአቻ ውጤቶች ስያስመዘግብ ከነዛ ጨዋታዎች ውስጥ በስድስቱ ግብ ሳያስቆጥር ወጥቷል። ቁጥሮችም እንደሚያመላክቱት ሰራተኞቹ ደካማ የፊት መስመር አላቸው። ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ድል ካደረገበት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም ሌላ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደውና በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘውን የፈረሰኞቹ ተከላካይ ክፍል እንደመግጠማቸው ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።
ከመሪው መቻል በሦስት ነጥቦች ዝቅ ብለው በ 3ኛ ደረጃነት የተቀመጡት ፈረሰኞቹ ደረጃቸውን ለማሻሻል አልመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታመናል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በነገው ጨዋታ ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም ከቡድኑ አካሄድ አንፃር የነገውን ጨዋታ ተገማች እንዳይሆን ያደርገዋል። በመጀመርያዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ካስመዘገቡት ተከታታይ ድል ወዲህ በተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት ፈረሰኞቹ በውጤት ረገድ ወጥነት ይጎድላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ላላቸው ክፍተት ከወዲሁ መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን ሦስት ለባዶ ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻለው በአንዱ ብቻ ነው። ይህም በሊጉ ጅማሮ ድንቅ የነበረው የማጥቃት ጥምረት መቀዛቀዙ አንድ ማሳያ ነው።
በወልቂጤ በኩል ለግል ጉዳይ አስፈቅዶ እስካሁን ድረስ ቡድኑን ያልተቀላቀለው አሜ መሐመድ በነገው ጨዋታ አይኖርም።በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ የሊጉ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋች ሀሮን አንተር በጉዳት ምክንያት በዚህ ጨዋታ ተሳትፎ አይኖረውም።
ቡድኖቹ እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ስድስት ድሎችን ሲያሳካ
ሦስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ፈረሰኞቹ 21 ሰራተኞቹ ደግሞ 9 ግቦች አስቆጥረዋል።
ወላይታ ድቻ ከ ሻሸመኔ ከተማ
ከተከታታይ የአቻና ሽንፈት ውጤቶች በኋላ ድል ለማድረግ አልመው ወደ ሜዳ የሚገቡትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ነገ ምሽት ይከናወናል።
በኢትዮጵያ ዋንጫ ፈረሰኞቹን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያሻግራቸውን ውጤት ያስመዘገቡት የጦና ንቦቹ በሀያ ሁለት ነጥቦች 8ኛ ደረጃን ይዘው የመጀመርያውን ዙር አገባደዋል። የጦና ንቦቹ በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ትልቅ የወጥነት ችግር ታይቶባቸዋል፤ ምንም እንኳ የቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መጥፎ የሚባል አይሁን እንጂ በውጤት ረገድ ግን ተከታታይነት አልነበረውም። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት፣ ሁለት የአቻና አንድ ድል አስመዝግቧል፤ ይህ ማለት ከጨዋታዎቹ ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ አስሩን ጥሎ ማሳካት የቻለው አምስት ብቻ ነው። አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በነገው ጨዋታ ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየት ችግር ያለበትና ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ላይ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለውን የፊት መስመራቸውን የአፈፃፀም ችግር ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።
ለአምስት ጨዋታዎች ከዘለቀው ያለመሸነፍ ጉዞ በኋላ ሁለት ሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሻሸመኔ ከተማዎች በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ። በአመዛኙ ወደ መከላከሉ ያደላ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድናቸው በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላለው ውስንነት መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ምንም እንኳ ከሁለቱ በወራጅ ቀጠናው ካሉ ቡድኖች የሚልቅ የግብ መጠን ቢያስመዘግብም በግማሽ የውድድር ዓመት በአንድ ጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻለው በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ነው። በቀጣይም በቅርብ ሳምንታት በጎ ለውጦች ያመጣው የተከላካይ ክፍል ውጤታማነት ማስቀጠልና የአጥቂ ክፍላቸው ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።
በወላይታ ድቻ በኩል ፀጋዬ ብርሃኑ እና ባዬ ገዛኸኝ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል፤ በሻሸመኔ በኩል ወጋየሁ ቡርቃ በቅጣት ቻላቸው መንበሩ ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አዲሱ ፈራሚ ስንታየው መንግስቱ በጨዋታው የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። ከክለቡ ጋር ለመለያየት መልቀቅያ ያስገባው አለን ካይዋም ከቡድኑ ጋር አይገኝም።
በአንደኛው ዙር ለሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ በነበረው የሊግ ግንኙነት ወላይታ ድቻ በፀጋዬ ብርሀኑ ብቸኛ ጎል 1-0 መርታት ችሏኀል።