ሻሸመኔዎች ከመመራት ተነስተው ወላይታ ድቻን 2ለ1 በማሸነፍ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።
በምሽቱ መርሐግብር ወላይታ ድቻ እና ሻሸመኔ ከተማ ሲገናኙ ወላይታ ድቻ በባህርዳር 1ለ0 ከተረታበት ስብስቡ አናጋው ባደግን በኬኒዲ ከበደ ፣ ባዬ ገዛኸኝን በብሥራት በቀለ ሲተኩ ሻሸመኔ በመቻል 1ለ0 ከተረታበት ጨዋታው ኬን ሰይዲን በአቤል ማሞ ፣ እዮብ ገብረማርያምን በአሸናፊ ጥሩነህ ፣ ወደ ሀገሩ አምርቶ መመለስ ባልቻለው አለን ካይዋ ምትክ አዲሱን ፈራሚ ስንታየሁ መንግሥቱ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
1፡00 ሲል 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ጀግኖችን በመዘከር በዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ድቻዎች ጨዋታው በተጀመረበት ቅጽበት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የዘላለም አባተን ወርቃማ የግብ ዕድል ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ እና ተከላካዩ ያሬድ ዳዊት አግደውበታል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም ብሥራት በቀለ ከዘላለም አባተ በተመቻቸለት ኳስ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች 16ኛው ደቂቃ ላይም በቢኒያም ፍቅሩ አማካኝነት ከረጅም ርቀት ጥሩ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ አስወጥቶበታል።
ቀስ በቀስ በተለይም ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሻሸመኔዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊቆጠርባቸው ተቃርቦ ፍጹም ግርማ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አብነት ደምሴ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ በሻሸመኔ ከተማዎች በኩል አሸብር ውሮ ከግራ መስመር አሻምቶት ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በመለሰው ኳስ አሸናፊ ጥሩነህ ጥሩ አጋጣሚ ቢያገኝም ኳሱን ሳይቆጣጠረው ቀርቶ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።
በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት የጦና ንቦቹ 39ኛው ደቂቃ ላይ በብሥራት በቀለ አማካኝነት ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ በእግሩ ሲመልስበት 45ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ኬኔዲ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሩ በጥሩ አጨራረስ በግራ እግሩ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ከዕረፍት መልስ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ተሻሽለው የቀረቡት ሻሸመኔ ከተማዎች 53ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። አብዱልቃድር ናስር ከቀኝ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ጌትነት ተስፋዬ በመጠኑ ከጨረፈው በኋላ ያገኘው ስንታየሁ መንግሥቱ ኳሱን በድንቅ አጨራረስ የቀድሞ ክለቡ መረብ ላይ አሳርፎታል።
በሁለተኛው አጋማሽ ከነበራቸው ከፍተኛ ግለት ተቀዛቅዘው የቀረቡት ድቻዎች የተሻለውን የመጀመሪያ ሙከራቸውን 64ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ቢኒያም ፍቅሩ ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ይዞበታል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ዮናታን ኤልያስ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ባሻማው ኳስ አበባየሁ ሀጂሶ በግንባር በመግጨት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።
የጨዋታውን ሂደት በግሩም ሁኔታ መቀየር የቻሉት ሻሸመኔዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሀብታሙ ንጉሤ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አሸናፊ ጥሩነህ ኃይል በሌለው ንክኪ በብልጠት አስቆጥሮታል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ስንታየሁ መንግሥቱ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝቶ በግራ እግሩ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር ተደርጎ 90+3ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው ዮናታን ኤልያስ ሞክሮት ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ከመለሰበት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳያስመለክተን ጨዋታው በሻሸመኔ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ያባከኗቸው ኳሷች ውጤት እንዲያጡ ምክንያት እንደሆናቸው በመናገር ግብ ያስተናገዱትም በማርኪንግ እና በኮምዩኒኬሽን ችግር መሆኑን ጠቁመው ተጫዋቾች ራስ ወዳድ ሆነው ያባከኑት ኳስ ዋጋ እንዳስከፈላቸው አበክረው ገልጸዋል። የሻሸመኔ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ በበኩላቸው በሁለተኛው አጋማሽ ትዕግስት የተሞላበት አጨዋወታቸው ግብ እንዲያስቆጥሩ እንዳገዛቸው በመናገር በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ማለማቸውን እና ዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጎ ግብ ያስቆጠረው ስንታየሁ መንግሥቱ ላይ የጠበቁትን ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።