የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ሳምንት መገባደጃ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና
በሀያ ስድስት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ሊጉ አናት የሚያስጠጋቸውን ነጥብ ፍለጋ ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ። ሀምበሪቾን በገጠሙበት የመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ላይ በአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ስር ለመጀመርያ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥሩ የወጡት ቡናማዎቹ ተጠባቂ በነበረው የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈው እንደመምጣታቸው ከፍ ባለ የስነ-ልቦና ደረጃ ሆነው ወደ ጨዋታው ይገባሉ ተብሎ ይገመታል። ቡናማዎቹ በሁሉም ረገድ ተሻሽለው በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛሉ። በተለይም ለተከታታይ አራት ሳምንታት ግቡን ያላስደፈረውና ከመጨረሻው የሊግ ሽንፈት በኋላ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ላይ ከአንድ ግብ በላይ ያላስተናገደው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በድንቅ ብቃት ላይ ይገኛል። ከዚ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመርም በኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ጭምር አራት ግቦች በማስቆጠር ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል።
በአስራ ስምንት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ቡናማዎቹን ይገጥማሉ። ሲዳማዎች ምንም እንኳ ከተከታታይ አራት ሽንፈት አልባ ሳምንታት በኋላ በሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት ብያስተናግዱም ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር ያሳዩት እንቅስቃሴ ግን መጥፎ የሚባል አይደለም። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሦስቱም በሊጉ አናት የሚገኙ ጠንካራ ቡድኖች ገጥሟል። ከመቻልና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአንድ የግብ ልዩነት ሽንፈት አስተናግዶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ድል አድርጓል። በነገው ጨዋታም በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውና በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘውን ኢትዮጵያ ቡና እንደ መግጠማቸው ቀላል ፈተና አይጠብቃቸውም። በተለይም በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር ከወጣ በኋላ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በጨዋታ በአማካይ 1.5 ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ መቅረብ ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በጉዳት ላይ ያሉትን የመሐመድኑር ናስር እና ጫላ ተሺታ ግልጋሎት አያገኙም። በሲዳማ ቡናዎች በኩል ደስታ ደሙ በጉዳት ብርሀኑ በቀለ ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አጥቂው ይገዙ ቦጋለም ከክለቡ ጋር አይገኝም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 27 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 9 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን በ10 ጨዋታ አቻ ተለያይተው 8 ጨዋታ ሲዳማ ቡና አሸንፏል። ኢትዮጵያ ቡና 34 ሲዳማ ቡና 28 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል። (መረጃው የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመንን አያካትትም)
ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት ለዓለም ዋሲሁን እና ኤልያስ መኮንን ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በበኩሉ አራተኛ ሆኖ ተመድቧል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አዳማ ከተማ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሊጉ አናት ለመቆናጠጥ አዳማ ከተማ ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ የሚካደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች
በሰላሣ ሁለት ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከሳምንታት በኋላ ዳግም ወደ መሪነት የመመለስ ዕድል በእጃቸው ላይ አለ። ቡድኑ ትናንት መሪው መቻን ሽንፈት ማስተናገዱ ተከትሎ ዳግም ወደ መሪነቱ የመመለስ ዕድል አለው፤ ሆኖም የነገ ተጋጣሚያቸው በውድድር ዓመቱ ሁለት ሽንፈቶች ብቻ ያስተናገደ ቡድን እንደመሆኑ ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም። ንግድ ባንኮች በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ላይ ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ድል አድርገዋል፤ ከድሉም በተጨማሪ በሁለት ጨዋታዎች ተዳክሞ የነበረው የቡድኑ የፊት መስመር ወደ ቀድሞ ጥሩ ብቃቱ ተመልሷል። ቡድኑ በሊጉ ጥሩ የመከላከል ቁጥሮች ካላቸው ክለቦች አንዱ የሆነውና በስምንት ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር በወጣው ፋሲል ከነማ ላይ አራት ግቦች ማስቆጠሩ የማጥቃት አጨዋወቱ ወደ ቀድሞ ጥሩ ብቃቱ መመለሱ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም ወደ መሪነት ለመምጣት ጥቂት ሽንፈት ካስተናገዱት ሁለት ክለቦች አንዱ የሆነውን አዳማ ከተማ ይገጥማል።
በሀያ ሦስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች በሊጉ ለተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠማቸውም፤ በሁለቱ ድል ስያደርጉ በአራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። በነገው ጨዋታም ሽንፈት አልባ ጉዟቸው ለማስቀጠልና ከፋሲል ከነማ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
አዳማዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ጠንካራ የፊት መስመር አላቸው፤ ቡድኑ ምንም እንኳ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር ቢወጣም ከዛ በኋላ ባከናወናቸው አራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች በማስቆጠር ጥንካሬውን መልሶ አግኝቷል። አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የነገው ተጋጣሚያቸው ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን እንደመሆኑ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ የተዳከመውን የተከላካይ ክፍላቸው ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ከስህተት የፀዳ መሆን ይጠበቅበታል።
በንግድ ባንክ በኩል ጉዳት ያሉትን ኪቲካ ጅማ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ብሩክ እንዳለና እንዳለ ዮሐንስ በነገው ጨዋታ የመሰለፍ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።
በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ችግር ውስጥ በሚገኙት አዳማ ከተማዎች በኩል ጥያቄ ካነሱት ተጫዋቾች መካከል ቻርልስ ሪባኑ እና አህመድ ረሺድ የመመለሳቸው ጉዳይ እንደ መልካም ዜና የሚወሰድ ነው።
በሊጉ 33 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባንክ 17 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። አዳማ 4 ጨዋታ ሲያሸንፍ በ12 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ባንክ 52 ጎሎች ሲያስቆጥር አዳማ 28 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።
ይህንን ጨዋታ ሔኖክ አክሊሉ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል እንስት ረዳት ዳኛ ወይንሸት አበራ እና ዘሪሁን ኪዳኔ ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በአንፃሩ አራተኛ ሆኖ ተሰይሟል።