ዛሬ በተደረጉ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ሶስት ጨዋታዎች ሀምበርቾ ፣ ልደታ ክፍለ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ረፋድ 3 ሰዓት ሲል ጅማሮውን ባደረገው መርሃግብር ሲዳማ ቡናን ከልደታ ክፍለ ከተማ ሲያገናኝ ጨዋታውም በልደታዎች የበላይነት የተፈፀመ ነበር።
ገና ከጅምሩ ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት ልደታዎች በ12ኛው ደቂቃ ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ ትመር ጠንክር ከመሀል ሜዳ አካባቢ በቀጥታ ወደ ግብ የላከችው ኳስ ሳይጠበቅ ወደ ግብነት ተቀይሮ ቡድኗ መሪ እንዲሆን አስችላለች።
ምንም እንኳን ግብ ቢያስተናግዱም ሲዳማ ቡናዎች በአንፃሩ ኳስን ተቆጣጥረው ወደፊት በመሄድ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም በተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለማየት የቻለ ሲሆን ያገኙትን አጋጣሚዎች ወደግብ ለመቀየር አብዝተው ሲጥሩ የነበሩት ልደታዎች በ60ኛው ደቂቃ አምበላቸው ህዳት ካሱ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ የሲዳማ ቡናን ተከላካዮች አታላ በማለፍ ግሩም ግብ አስቆጥራ መሪነታቸውን አስፍታለች።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተስፋ ሳይቆርጡ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት ሲዳማ ቡናዎች በ84ኛው ደቂቃ ቤዛዊት ንጉሴ ከሽንፈት ያልታደገቻቸውን ግብ ከግብ ክልል ውጪ በቀጥታ በማስቆጠር ጨዋታው 2ለ1 እንዲጠናቀቅ ሆኗል።
ቀን ስምንት ሰዓት ላይ በተከናወነ ጨዋታ ሀምበርቾ ከተማ ይርጋጨፌ ቡናን በመርታት ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።
ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጀሞረው ከፍ ያለ ጫና በማሳደር ወደፊት ገፍተው ሲጫወቱ የነበሩት ሀምበርቾዎች እስከ 35ኛ ደቂቃ በተደጋጋሚ ለግብ የተቀረቡ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም መጠቀም አልቻሉም።
በ35ኛው ደቂቃ ግን ሄለን መንግስቱ ከርቀት አክርራ የመታቸው ኳስ ከመረብ ጋር በመዋሀዱ ሀምበርቾን መሪ ማድረግ ችላለች።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መረጋጋት የተሳናቸው ይርጋጨፌ ቡናዎች በ39ኛው ደቂቃ የሰሩትን ስህተት በመጠቀም የተከላካይ መስመር ተጫዋች የሆነችው ብዙአየሁ አበራ ግብ አስቆጥራ መሪነታቸውን አስፍታ ወደመልበሻ ክፍል እንዲመለሱ አደርጋለች።
ከመልበሻ ክፍል መልስም ሀምበርቾዎች ጥንካሬያቸውን ያስቀጠሉ ሲሆን ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ሙከራዎችን አድርገዋል።ይርጋጨፌዎች በአንፃሩ በሁለቱም አጋማሾች ፍፁም ደካማ እንቅስቃሴን አድርገዋል።
በ80ኛው ደቂቃ የሀምበሪቾዋ ብርሃን ኋ/ስላሴ በቅብብል የተገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር ስታዋህድ ይርጋጨፌዎች ከባዶ መሸነፍ የታደገችውን ግብ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ሜሮን ገነሞ አስቆጥራ ጨዋታው በሀምበሪቾን የ3-1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
የሳምንቱ ማሳረጊያ በነበረው ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን የረታበት ነበር።
በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን በሁለቱም አጋማሾች ባሳየን ጨዋታ የተሻለ የውሳኔ አሰጣጥ ብንመለከት በብዙ ግቦች በተንበሸበሸበ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማዎች መጠነኛ የበላይነት በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ የተቋጨ ነበር ፤ በሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ ግለሰባዊ ለውጦችን ያደረጉት አዲስ አበባዎች በኳስ ቁጥጥር እና በግብ ሙከራ የተሻሉ ነበሩ።
በ59ኛው ደቂቃ ኳስን ይዘው ወደ ተቃራኒ ሳጥን የደረሱት አዲስ አበባዎች መዲና ዐወል በግሩም ሁኔታ ባስቆጠረቻት ግብ ቀዳሚ መሆን ሲችሉ በ95ኛው ደቂቃ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ አይናለም ዓለማየሁ በግል ጥረቷ ከመረብ በማዋሀድ ቡድኗ ጨዋታውን 2-0 በሆነ ውጤት እንዲያሸንፍ አስችላለች።