በጨዋታ ሳምንቱ የሚሳረጊያ መርሃግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በመርታት ዳግም የሰንጠረዡን አናት በመቆናጠጥ የጨዋታ ሳምንቱን ፈፅሟል።
አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ መርሃግብር ከተጠቀሙት ስብስብ ሁለት ለውጦችን ሲያደርጉ ታዬ ጋሻው እና ፉዓድ ኢብራሂምን አሳርፈው በምትካቸው አህመድ ረሺድ እና ሳዲቅ ዳሪን ሲያስገቡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ደግሞ ከመጨረሻው ስብስባቸው
ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አቤል ማሙሽን በቢኒያም ጌታቸው ብቻ በመተካት ወደ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
በጨዋታው ፈጠን ያለ አጀማመርን ማድረግ የቻሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በጨዋታው ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ያገኙት ገና በማለዳ ነበር ፤ በጨዋታው ቀዳሚ የግብ ሙከራ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተጋጣሚ ሜዳ ከነጠቁት ኳስ መነሻውን ባደረገ የማጥቃት ሂደት ባሲሩ ዑመር ከግራ የሳጥን ክፍል አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ኪቲካ ጅማ በቀላል ንክኪ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
ከግቧ መቆጠር በኃላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት አዳማዎች በተሻለ መልኩ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም በማጥቂያው ሲሶ የነበራቸው አፈፃፀም ግን ፍፁም ደካማ ነበር።
በአንፃሩ ንግድ ባንኮች ደግሞ ፈጠን ባሉ ቀጥተኛ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በተለይም በ15ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሱሌይማን ሀሚድ ከቀኝ መስመር በግል ጥረቱ ወደ ወስጥ ይዞ የገባውን ኳስ ለቡድን አጋሩ አዲስ ግደይ ቢያቀብለውም አዲስ ያመከናት እንዲሁም በ19ኛው ደቂቃ ቢኒያም ጌታቸው በፈጣን ሽግግር ያገኘውን ኳስ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ አህመድ ረሺድ ያቋረጠበት ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ።
ነገርግን በ22ኛው ደቂቃ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው የቆዩት አዳማዎች አቻ መሆን ችለዋል ፤ ቢኒያም አይተን ያደረሰውን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ በሳጥኑ ጠርዝ ተቆጣጥሮ በግሩም አጨራረስ የቡድኑን የአቻነት ግብ አስገኝቷል።
በደቂቃዎች ልዩነትም ተስፈኛው አማካይ ሳዲቅ ዳሪ የአዳማን መሪነት ለማሳደግ ከሳጥን ውጭ ግሩም ሙከራን ቢያደርግም ፍሬው ጌታሁን ኳሷን ይዞበታል።
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር ይበልጥ ምልልሶች በበዙት አጋማሹ ምንም እንኳን የጠሩ የግብ ዕድሎችን ባንመለከትም በሁለቱ ቡድኖች በኩል በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የተከወነ ነበር ፤ ነገርግን ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አጋማሹ ሊጠናቀቅ የሰከንዶች እድሜ ሲቀሩት በረከት ግዛው ከቀኝ መስመር የተጣለለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ በማስቆጠር ቡድኑ 2-1 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አስችሏል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጫና ፈጥረው ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ንግድ ባንኮች በአጋማሹ የመጀመሪያ ጥቂት ደቂቃዎች ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን በኪቲካ ጅማ እና አዲስ ግደይ በማድረግ ነበር የከፈቱት።
በሂደት ግን ፍፁም እየተቀዛቀዘ በመጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ60ኛው ደቂቃ አዳማ ከተማዎች ከቆመ ኳስ በፈጠሩት እና ታዬ ጋሻው በግንባሩ ከሞከረው ኳስ ውጭ በሙከራዎች ረገድ በተቀዛቀዘው አጋማሹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ግን ዳግም በ63ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ማሳደግ ችለዋል።
ቢኒያም ጌታቸው ከፍቅሩ ዓለማየሁ ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ግብ ክልሉን ለቆ ከወጣው ሰዒድ ሀብታሙ አናት በላይ በማሳለፍ ግሩም ግብን በማስቆጠር የንግድ ባንክን መሪነት ወደ 3-1 ከፍ ማድረግ ችሏል።
በቀሪዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በርከት ላሉ ተጠባባቂ ተጫዋቾቻቸው የጨዋታ ደቂቃን በመስጠት የጨዋታን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ላይ ባተኮረ መልኩ ሲንቀሳቀሱ አውንታዊ የሚመስሉ ለውጦችን ለማድረግ የሞከሩት አዳማ ከተማዎች በተለይ በመጨረሻዎች 15 ደቂቃዎች ወደ ንግድ ባንክ ሳጥን ቀርበው መጫወት ቢችሉም የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ ያደረጉት ጥረት በቂ አልነበረም።
ይባስ ብሎ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሳይሞን ፒተር የሰይድ ሀብታሙ ከግብ ክልል ለቆ መውጣቱን ተመልክቶ ከራሱ የሜዳ አጋማሽ በቀጥታ በመምታት ባስቆጠራት ግብ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ4-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ በዚህም ውጤት ንግድ ባንክ ዳግም የሰንጠረዡን አናት ከመቻል መረከብ ችለዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የአዳማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥሩ ጥረት ቢያደርጉም በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠረችባቸው ግብ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ያነሱ ሲሆን በተለይ የተከላካይ መስመራቸው ላይ በነበረው እንቅስቃሴም እንዲሁ ደስተኛ እንዳልነበረ ገልፀዋል ፤ በአንፃሩ የንግድ ባንክ አቻቸው አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በፍጥነት ወደ ጨዋታው መግባታቸው ለድል እንዳበቃቸው አንስተው በሁለቱም አጋማሽ በማጥቃት ሆነ መከላከል የነበራቸው ሚዛን ጥሩ እንደነበር አንስተዋል።