የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር አስረኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በግብ ተንበሽብሾ በማሸነፍ ከቀሪዎቹ የሳምንቱ ጨዋታዎች በፊት የሊጉ መሪነትን ሲረከብ መቻልም አሸንፏል።
ረፋድ ሦስት ሰዓት ላይ በጀመረው ጨዋታ መቻል ከአዳማ ከተማ የተገናኙ ሲሆን መቻሎች ባለቀ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፋክክር ባስመለከተው በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያሉ ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን አግንተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።
መቻል የግብ እድል በመፍጠር አኳያ የተሻሉ ነበሩ። አዳማ ከተማም አለፈው አለፈው የሚያገኟቸውን ኳሶች ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም ጠንከራውን የመቻል ተከላካይ መስመር አልፈው ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በዚህም የመጀመሪያ አጋማሽ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደመልበሻ ክፍል ለመመለስ ተገደዋል።
በሁለተኛው አጋማሽም የአንደኛው አጋማሽ ዓይነት ጥሩ ፉክክር ቢታይም አዳማ ከተማ የመከላከል ባህርይ ይዞ ሲገቡ መቻሎች በበኩላቸው ጫና ፈጥረው ግብ ለማስቆጠር በአንድ ለአንድ ቅበብል ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲገቡ ለመመልከት ተችሏል።
በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያደረጉት መቻሎች በኳስ ቁጥጥር ከተቃራኒ ቡድን ብልጫ ወስደዋል። አዳማ ከተማ በአንፃሩ ግብ ለማስቆጠር ኳስን ወደፊት ከመጫወት ይልቅ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት የፈለጉ በሚመስል መልኩ ወደኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ታይተዋል።
ግብ ሳይቆጠር መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃዎች ሲቀሩት በ85ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ንግስት በቀለ ከመስመር አከባቢ የተሻገረላትን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ከመረብ ጋር አገናኝታ ለመቻል ሶስት ነጥብ አስገኝታለች።
ቀን 10:00 ላይ በተደረገ መርሃ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከልደታ ክ/ከተማ ተገናኝቶ ኢትዮ በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፏል። ጨዋታው ገና ከመጀመሩ የግብ ሙከራዎች መደረግ በጀመሩበት በዚህ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከፍፁም ጨዋታ በላይነት ጋር ማሸነፍ ሲችል ከ6ኛው ደቂቃ ጀምሮ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
በ6ኛው ደቂቃ ፀጋነሽ ወራና ከሲሳይ ገ/ዋህድ ጋር በአንድ ለአንድ ያገኙትን ኳስ ከመረብ አገናኝታ ቀዳሚ ኢትዮ ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችላለች። ግብ ተቆጥሮባቸው መረጋጋት የተሳናቸው ልደታዎች ኳስን መሃል ሜዳ ላይ ጀምሮ በሰሩት ስህተት የተገኘችውን አጋጣሚ ተጠቅማ በ8ኛው ሲሳይ ገ/ዋህድ በራሷ ጥረት ኳስን ይዛ ወደ ግብ ክልል በመግባት በግሩም አጨራረስ ከመረብ ጋር አገናኝታ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ማድረስ ችላለች።
በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ጨዋታውን 2ለ0 መምራት የቻሉት ኤልፓዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሙከራ ሲያድርጉ ታይተዋል። ልደታ ክ/ከተማም በአንፃሩ ወደ ጨዋታ በመመለስ ኳስን ተቆጣጥረው ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል። ከዚህ ግብ ሙከራ በኋላም በ30ኛው ደቂቃ መአዛ አብደላ ከግብ ክልል ውጭ ሆኖ የተመታውን ኳስ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ ለመቆጠጣር ከብዷት ከእጇ ያመለጣትን ኳስ አግንታ ከመረብ ጋር አገናኝታ 2ለ1 በማድረግ ወደጨዋታ እንዲመለሱ አድርጋለች።
ልደታ ክ/ከተማዎች ግብ ካስቀቀጠሩ በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በጫና የተጫወቱ ቢሆንም ሌላ ግብ ሳያስቆጠሩ 2ለ1 እየተመሩ እረፍት ለመውጣት ተገደዋል።
ከአንደኛው አጋማሽ አንፃር የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብለው የገቡት ኤልፓዎች በኳስ ቁጥጥር ከተቃራኒ ቡድን የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። በ59ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው የምስራች ላቀው ርቀት ላይ ሆና አክሪራ የመታችውን ኳስ የልደታ ክ/ከተማ ግብ ጠባቂ በቀላሉ ለመቆጣጠር ጥረት ብታደርግም በእጆቿ መከካል ሾልኮ ወደግብነት ተቀይሮ ኤልፖዎችን ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ በላይነት እንዲወስዱ አድርጓል።
እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ በጫና የተጫወቱት ኤልፖዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ሌላኛዋ ተቀይራ የገባችው አንጋፋዋ ተጫዋች ሽታዬ ሲሳይ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ አግንታ አስቆጥራ መቻል 4ለ1 እንዲመራ አስቻላለች።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ውስጥ ሽታዬ ሲሳይ በራሷ ጥረት ከመሃል ሜዳ አከባቢ ኳስን እየገፋች በመሄድ የልደታን ተከላካዮች አታላ በማለፍ አምስተኛውን ግብ አስቆጥራ መቻሎች በሰፊ ግብ ልዩነት ልደታን አሸንፎ መሪነቱን በመረከብ ጨዋታው ተገባዷል።