መረጃዎች| 67ኛ የጨዋታ ቀን

በአስራ ሰባተኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

አዳማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ለሦስት ጨዋታዎች ከራቃቸው ድል ለመታረቅ ወደ ሜዳ የሚገቡ ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በመጨረሻው ጨዋታ የውድድር ዓመቱን ሦስተኛ ሽንፈት ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች በሃያ ሦስት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። አዳማዎች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም ፤  ከዛ በተጨማሪም ካለፉት አስር ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት በሁለቱ ብቻ ነው። በነገው ጨዋታም ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚገኘውን ወላይታ ድቻን ይገጥማሉ።  ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ተወጥረው ጨዋታዎቻቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙት አዳማዎች በውጤት ረገድ የወጥነት ችግር ቢኖራቸውም የቡድኑ እንቅስቃሴ ግን ተስፋ ሰጪ ነው። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ማስቆጠሩም የዚ ማሳያ ነው። ሆኖም ለስህተቶች ተጋላጭ እየሆነ የመጣው እና በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ስር ነቀል ለውጥ ይሻል።

በሀያ ሁለት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ። የጦና ንቦቹ ከጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በዘለለ ውጤት ይዘው ለመውጣት ተቸግረዋል። ቡድኑ ሁለት ተከታታይ ድል ካስመዘገበበት ወቅት በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት፣ አንድ ድልና ሁለት የአቻ ውጤቶች ማስመዝገቡም የውጤታማነት ደረጃው ማሽቆልቆሉን ይሳያል። ለዚ እንደ ዋነኛ ምክንያት ከሚነሱ ክፍተቶች አንዱ ደግሞ ለበርካታ ጊዜያት ሳይፈታ የቆየው የቡድኑ የግብ ማስቆጠርና የአፈፃፀም ችግር አንዱ ነው።
ቡድኑ ምንም እንኳ በሊጉ አስራ ስድስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ከሚፈጥራቸው በርካታ የግብ ዕድሎች የሚመጣጠን የግብ መጠን ማስመዝገብ አልቻለም። ከዚ በተጨማሪ የግብ ማስቆጠር ኃላፊነቱ የቡድኑ ሀምሳ በመቶ ግቦች ባስቆጠረው ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም ፍቅሩ የተንጠለጠለ መሆኑም እንደ ምክንያት ሊነሳ ይችላል። በሊጉ ጥሩ የአማካይ ጥምረት ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆነውን ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በቀጣይ ጨዋታዎች የፊት መስመር ችግራቸውን የመቅረፍ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።

በወላይታ ድቻ በኩል ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ የነበሩት ፀጋዬ አበራ እና ባዬ ገዛኸኝ በተመሳሳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በአንፃሩ በአዳማ ከተማ በኩል ቻርልስ ሪባኑ ዳግም ከክፍያ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ከነገው ስብስብ ውጭ ሲሆን መጠነኛ ህመም ላይ የሚገኘው ኤልያስ ለገሰም የመሰለፍ ዕድሉ አጠራጣሪ መሆኑ ተረጋግጧል።

እያሱ ፈጠነ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመራዋል፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሠ እና አብዱ ይጥና ረዳቶች ፤ ሔኖክ አክሊሉ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።

19 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 9 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 7 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪው ሦስት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ድቻ 21፣ አዳማ 17 አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም)

ሲዳማ ቡና ከ ወልቂጤ ከተማ

ከተከታታይ ሽንፈቶች ለመላቀቅ ወደ ሜዳ የሚገቡትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት ላይ ይደረጋል።

በአስራ ስምንት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች ለማገገም ወልቂጤ ከተማን ይገጥማሉ። ሲዳማ ቡናዎች ባለፉት አራት ጨዋታዎች በሰንጠረዡ አናት የሚገኙ ቡድኖችን ገጥመው ሦስት ሽንፈትና አንድ ድል አስመዝግበዋል። ቡድኑ ከአራት ተከታታይ ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በተከታታይ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ደረጃው አሽቆልቁሏል። ከዛ በተጨማሪ ቡድኑ በጥሩ የውጤታማነት ጉዞ በነበረበት ወቅት ለተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ወጥቶ የነበረው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት በቅርብ ሳምንታት ጥንካሬውን አጥቷል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎችም ዘጠኝ ግቦች አስተናግዷል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የቡድኑን የቀደመ የመከላከል ጥንካሬ ከመመለስ በተጨማሪ ላለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስቆጠረው የፊት መስመራቸውም ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ለዘጠኝ ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ወልቂጤ ከተማዎች በአስር ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሠራተኞቹ ተከታታይ ሽንፈቶች ከማስተናገድ ባለፈ ግቦች ለማስቆጠርም ተቸግረዋል፤ በውድድር ዓመቱ ስድስት ግቦች ብቻ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ድል ካደረገበት ጨዋታ በኋላ ባካሄዳቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን ሁለት ብቻ ነው። ከጥቂት ጨዋታዎች ውጭ በአመዛኙ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት የሚያደርግ ቡድን የገነባው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት አጨዋወቱ በቁጥርም ሆነ በጥራት ላቅ ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር እንዲችል በማጥቃት አጨዋወቱ ለውጦች ማድረግ ይኖርበታል።


በሲዳማ ቡና በኩል ጉዳት ላይ የቆየው ደስታ ደሙ መሰለፉ አጠራጣሪ ሲሆን ብርሀኑ በቀለ ከቅጣት ተመልሷል። አጥቂው ይገዙ ቦጋለም ክለቡን ተቀላቅሏል። ወልቂጤዎች በቅጣትም በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሙሉቀን ያረጋል በመሐል ዳኝነት አስቻለው ወርቁ እና ዘሪሁን ኪዳኔ ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ አራተኛ ሆኖ ተመድቧል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 7 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 3 በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ሦስት ጊዜ አቻ ወጥተው በአንዱ ወልቂጤ አሸንፏል። ሲዳማ ቡና 6፣ ወልቂጤ 4 አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም)