ዳዊት ተፈራ ደምቆ ባመሸበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀምበሪቾን በመርታት በሰንጠረዡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ያሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻ ጨዋታ ወልቂጤን ሲረቱ በተጠቀሙበትን የመጀመሪያ 11 ተመራጮች ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የዛሬውን ጨዋታ ሲጀምሩ በአንፃሩ ሀምበሪቾዎች በኩል ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ ከተረታው ስብስብ ሶስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ታየ ወርቁ ፣ ምናሴ ቢራቱ እና አላዛር አድማሱን አስወጥተው በምትካቸው ትዕግስቱ አበራ ፣ አብዱሰላም የሱፍ እና ዳግም በቀለን በማስገባት ጀምረዋል።
በዝናባማ የአየር ፀባይ ታጅቦ በተከወነው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሙከራዎችም ረገድ ፍፁም የተቀዛቀዘ አጀማመርን ያስመለከተን ነበር ፤ በቅዱስ ጊዮርጊሶች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በጀመረው ጨዋታው የግብ ዕድሎችን ለመመልከት ብዙ ደቂቃዎችን ለመጠበቅ የተገደድንበት ነበር።
ፍፁም ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ባስመለከተን ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር በተወሰነ መልኩ ጫናዎችን ማሳደር የጀመሩ ሲሆን በዚህም በ29ኛው ደቂቃ መሪ መሆን ችለዋል ፤ ዳግማዊ አርዓያ ላይ ምንያምር ጴጥሮስ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ ዳዊት ተፈራ በማስቆጠር ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
በሀምበሪቾዎች በኩል እንደ ቡድን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ውስንነቶች የነበሩባቸው ቢሆንም በግሉ በተለይ በቀኝ መስመር ጥሩ ጥረቶችን ሲያደርግ የነበረው ቶሎሳ ንጉሴ በ33ኛው ደቂቃ ካደረጋት የቡድኑ ብቸኛ የአጋማሹ ሙከራ ባለፈ ጥረቱ የሚደነቅ ነበር።
መሪ ከሆኑ በኃላ በተወሰነ መልኩ የተነቃቁ የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ42ኛው ደቂቃ በግሩም የቅብብል ሂደት ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ ቢኒያም በላይ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት ተፈራ ለእራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በፈረሰኞቹ የ2-0 መሪነት ወደ ዕረፍት እንዲያመራ አስችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሶስት ተጫዋቾችን ቀይረው በማስገባት ሀምበሪቾዎች የጀመሩ ቢሆንም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የተለየ ነገርን ሜዳ ላይ ለማሳየት የተቸገሩበት ነበር።
በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በ54ኛው ደቂቃ አማካዩ በረከት ወልዴ ባጋጠመው ጉዳት በፍሪምፖንግ ኩዋሜ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት የተገደደ ሲሆን በአጋማሹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ኳሱን መቆጣጠር ቢችሉም ለአጥቂዎች ይላኩ የነበሩት የመጨረሻ ኳሶች በተወሰነ መልኩ ጥራት የጎደላቸው በመሆኑ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ለማፍራት ብዙ ለመጠበቅ ተገደዋል።
በአጋማሹ ቢኒያም በላይ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና የግቡ አግዳሚን ለትማ ወደ ውጭ የወጣችበትን ሙከራ ያደረገ ሲሆን በ75ኛው ደቂቃ ግን ታምራት እያሱ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ያሳለፈለትን ኳስ በፍፁም መረጋጋት ከተቀበለ በኃላ በጥሩ አጨራረስ የቡድኑን መሪነት ያሳደገችውን ግብ አስገኝቷል።
ፍፁም ደካማ የጨዋታ ዕለትን ያሳለፉት ሀምበሪቾዎች በጨዋታው መደበኛ ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ላይ ባደረጉት የመጀመሪያው ዒላማውን በጠበቀው ሙከራቸው በቶለሳ ንጉሴ አማካኝነት የማስተዛዘኛዋን ግብ ያገኙ ሲሆን በዚህም ጨዋታው በፈረሰኞቹ የ3-1 የበላይነት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበሪቾው ጊዜያዊ አሰልጣኝ መላኩ ከበደ ከውጤት በዘለለ ከተጋጣሚያቸው ጥራት አንፃር ጥሩ ስለመንቀሳቀሳቸው ሲገለፁ በአንፃሩ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው በተጫዋቾቻቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው በጨዋታው ግባቸውን ሳያስደፍሩ አለመውጣታቸው በተወሰነ መልኩ ቅር እንዳሰኛቸው የገለፁ ሲሆን አሁን ቢሆን ከፊት ስለሚጠብቋቸው ጨዋታዎች እንጂ ስለደረጃቸው ብዙም እንደማይጨነቁ ተናግረዋል።