የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ የምድብ ሀ የሁለተኛ ቀን ሦስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይርጋጨፌ ቡና በሰፊ ግብ ልዩነት ሲያሸንፍ ኦሮሚያ ፖሊስም አሸንፏል።
ረፋድ 3:00 ስልጤ ወራቤን ከኦሮሚያ ፖሊስ ያገናኘው መርሃግብር በኦሮሚያ ፖሊስ በላይነት ሲጠናቀቅ ኦሮሚያ ፖሊስ በመጀመሪያ አጋማሽ ያገኙትን አጋጣሚ በሚገባ በመጠቀም የሶስት ነጥብ ባለቤት መሆን ችለዋል።
እምብዛም የግብ ሙከራ ባልታየበት በዚህ ጨዋታ ኦሮሚያ ፖሊስ በ16ኛው ደቂቃ በእርስ በርስ በመግባት ከፍፁም ቅጣት ምት መምቻ ውጪ በመሆን ኃይሌ ዘመድኩን ግሩም ግብ አስቆጥሮ መሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ስልጤ ወራቤ አልፈው አለፈው ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው የነበረ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው በኦሮሚያ ፖሊስ 1ለ0 መሪነት ወደመልበሻ ክፍል ገብተዋል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ ሁለቱም ቡድኖች ቀዝቀዝ ያለ የጨዋታ እንቅስቃሴና ደካማ የኳስ ቅብብል የታየበት ጨዋታ ነበር። ኦሮሚያ ፖሊስ መሪነቱን ለማስጠበቅ በመከላከል ሲጫወቱ ወራቤዎች አቻ ለመሆን የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ሆኖም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው በኦሮሚያ ፖሊስ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ስምንት ሰዓት ላይ የተደረገው የኮልፌ ቀራኒዮ እና የነቀምቴ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ጥፋቶች በበዙበት በዚህ ጨዋታ በ4ኛው ደቂቃ ነቀምቴ ከተማ ረጅም ኳስ የጣሉትን የኮልፌ ቀራኒዮ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ ለማውጥት ጥረት ሲያደርጉ በተፈጠረው አለመግባባት ውበት አብተው በራሱ ግብ ላይ ኳሷን አሳርፎ ነቀምቴ ከተማን ቀዳሚ እንዲሆኑ አድርጓል።
ኮልፌ ቀራኒዮ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር አብዝተው ጥረት አድርገዋል። በ34ኛው ደቂቃም በቅብብሎሽ የተገኘውን ኳስ አኩየር ቻም ከመረብ ጋር አገናኝቶ አቻ ሆኖ የመጀመሪያው አጋማሽ 1ለ1 ሊጠናቀቅ ችሏል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ የተቀዛቀዘ ጨዋታ የነበረ ሲሆን ብዙም የግብ ሙከራ ሲያደርጉ ለመመለከት አልተቻለም። ሆኖም ግን ኮልፌዎች በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የሆኑበትን ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል። ነቀምቴ ከተማ በአንፃሩ አልፎ አልፎ ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን ቢያገኝም ለማስቆጠር ሲዳግታቸው ተስተውለዋል። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለከቱ ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች አንድ እኩል በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ከዝናብ ጋር የታጀበው የ10:00 ጨዋታ ሞጆ ከተማን ከይርጋጨፌ ቡና አገናኝቶ ይርጋጨፌ ቡና በሰፊ ግብ ልዩነት 3-0 መርታት ችለዋል።
ጨዋታው እንደተጀመረ በኳስ ቁጥጥር በልጠው የተገኙት ይርጋጨፌ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር ፍፁም በላይነት ወስደው ግቦችን ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል። በ25ኛው ደቂቃ አቤነዘር ከፍያለው ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ መጥቶ ግብ አስቆጥሮ ቀዳሚ አድርጓቸዋል።
ሞጆ ከተማ በአንፃሩ ደካማ የሚባል የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። እንዲሁም ብርሃኑ ወልቂቶ የይርጋጨፌ ቡናውን ተመስገን ሀይሉን በክድኑ በመምታት በሰረው ጥፋት በ35ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። በዚህም ቀሪውን ደቂቃ በጎዶሎ ቁጥር ለመጫወት ተገደዋል። ክፍተቱን የተጠቀሙት ይርጋጨፌ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ታይተዋል። ሆኖም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያ አጋማሽ በ1ለ0 እየመሩ መውጣት ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብለው የገቡት ይርጋጨፌዎች ተቀራኒ ቡድኑ ጎዶሎ መሆኑን በመጠቀም ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥረዋል። በ51ኛው ደቂቃ ፈቲ ረሃም በአንድ ለአንድ ቅብብል ያገኙትን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪነታቸውን አስፍቷል።
ሁለተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መረጋጋት የተሳናቸው ሞጆዎች የሰሩትን ስህተት በመጠቀም በ54ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ ፈቲ ረሃም አስቆጥሮ ጨዋታውን መጨረስ ችሏል። ይርጋጨፌዎች እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የታዩ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 3ለ0 በሆነ ውጤት በይርጋጨፌ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።