የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ቀሪ 5 ጨዋታዎች ትላንት ተካሂደው መከላከያ ወደ ሊጉ መሪነት ያመጣውን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ 9፡00 ላይ በተደረገው ጨዋታ ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው መከላከያነ የድል ግብ ያስቆጠረው አጥቂው መሃመድ ናስር ነው፡፡ ጦሩ ድሉን ተከትሎ ከ7 ጨዋታዎች 13 ነጥቦችን ሰብስቦ ካለሽንፈት ሊጉን መምራት ጀምሯል፡፡

ይርጋለም ላይ ለአንድ ሳምንት ሊጉን ሲመራ የነበረው ሲዳማ ቡና ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በሜዳው ተሸንፏል፡፡ የአዳማን የድል ግቦች ቢንያም አየለ እና ሱሌይማን ሞሃመድ ሲያስቆጥሩ 2 ተጫዋቾች ከአዳማ በኩል ከሜዳ በቀይ ካርድ ተወግደዋል፡፡

ወደ አሰላ የተጓዘው አርባምንጭ ከነማ ሙገር ሲሚንቶን 1-0 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ለአርባምንጭ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው አምበሉ ሙሉአለም መስፍን ነው፡፡

ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ወልድያን አሸንፎ ወደ ላይ ከፍ ማለቱን ተያይዞታል፡፡ የወላይታ ድቻን የድል ግቦች ባዬ ገዛኸኝ እና ዮሴፍ ዴንጌቶ ከመረበ አሳርፈዋል፡፡ አዲስ መጪው ወልድያ እስካሁን ካደረጋቸው 7 ጨዋተዎች ምንንe ድል ሳያስመዘግብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል፡፡

የሳምቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው በንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የተደረገው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ፈረሰኞቹ ናትናኤል ዘለቀ ከመረብ ባሳረፈው ግብ እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ድረስ ሲመሩ ቢቆዩም በ89ኛው ደቂቃ ላይ በኤፍሬም አሻሞ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፊሊፕ ዳውዚ ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑንe ከሽንፈት ታድጓል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉን ሙሉ 7 ጨዋታ ያደረገው መከላከያ በ13 ነጥቦች ሲመራ እርስ በእርስ ቀሪ ጨዋታ ያላቸው መብራት ኃይል እና ኢትዮጵያ ቡና በእኩል 12 ነጥቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ሳሚ ሳኑሚ በ6 ፣ ቢንያም አሰፋ በ5 ይከተላሉ፡፡

 

ያጋሩ