በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ሀ” በሦስተኛ ቀን ቀጥለው በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የምድቡ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነቱን ማጠናከር የሚችልበትን አጋጣሚ ሳይጠቀም ሲቀር አዲስ አበባ ከተማ አሸንፏል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የምድቡ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሀላባ ከተማን ገጥሟል።
በጋለ የጨዋታ ስሜት በጀመረው በዚህ ጨዋታ ሀላባ ከተማ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ኤሌክትሪኮችም መሪነታቸውን ለማጠናከር በመልሶ ማጥቃት በጥሩ ኳስ ቅብብል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል ሲገቡ ተስተውለዋል።
የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አቤል ሀብታሙ 12ኛው ደቂቃ ምናልባትም ግብ ማስቆጠር የሚችልበትን ኳስ ይዞ በሚገባበት ቅፅበት የሀላባ ከተማው አምበል አብዱልከሪም ረማቶ ከኋላ በመግባት በሠራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ከዚህ በኋላ ቀሪውን ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሙከራ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ችለዋል። ሆኖም ግን በጎዶሎ ሲጫወቱ የነበሩት በርበሬዎቹ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመጫወታቸው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል።
በ44ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪኮች አደገኛ ሙከራ ሚባለውን በአቤል ሀብታሙ አማካኝነት ያደረጉ ሲሆን ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ሆኖም ያለ ምንም ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሀላባን ቁጥር ማነስ በመጠቀም ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ቢችልም ጠንካራ ሆኖ የዋለውን የሀላባን ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ማስቆጠር ከብዷቸዋል። እንዲሁም ከርቀት የሚያደርጓቸውን ጠንካራ ሙከራዎች የሀላባው ግብ ጠባቂ ሲመልስባቸው ተስተወሏል።
ሀላባ ከተማም በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ሙከራዎችን አድርጓል። ዒላማውን የጠበቀ አደገኛ ሙከራ በ87ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ኡመድ ኡኝቲቲ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ያደረገው ሙከራ ለትንሽ በግቡ አግዳሚ በኩል አልፋበታለች።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በርከት ያለ የግብ ሙከራ አድርጓል። መሳይ ሰለሞን ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በግብ አግዳሚ ለጥቂት የወጣበት ኳስ የመጨረሻው አደገኛ ሙከራ ሆና ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
5 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከጅማ አባቡና ያገናኘው መርሐግብር ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ግቦች አዲስ አበባ ከተማ አሸንፏል።
ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ባላስመለከተው የሳምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ደካማ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። በጨዋታውም ሁለቱም ቡድኖች ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን አዲስ አበባ ከተማ በኳስ ቁጥጥር ከተጋጣሚው ተሽሎ የተገኘበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ለመመለከት ተችሏል።
ጅማ አባ ቡና በአንፃሩ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፉ ሲሆን አለፎ አልፎ የሚያገኟቸውን ኳሶች ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ለመመልከት ተችሏል። ሆኖም ምንም ዒላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሳያስመለክቱ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጠንክረው መመለስ የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ቶሎ ቶሎ ወደተቃራኒ ቡድን ሲደርሱ ለመመልከት ተችሏል። እንዲሁም ከተጋጣሚው የተሻለ በርከት ያለ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።
ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ77ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ኃይሉ ተቀይሮ ከገባው ከቧይ ኩዌት የተሻገረለትን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ አዲስ አበባ ከተማ መሪ እንዲሆን አድርጓል። እንዲሁም ግብ ተቆጥሮባቸው መረጋጋት የተሳናቸውን የጅማ አባ ቡናን ክፍተት በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ለመመለከት ተችሏል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው አማኑኤል አሊሶ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ግሩም ግብ አስቆጥሮ አዲስ አበባ ከተማ 2ለ0 አሸንፎ እንዲወጣ አድርጓል።