በ17ኛው የጨዋታ ሳምንት ጎልተው በወጡ ተጫዋቾች ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።
አሰላለፍ 4-1-2-3
ግብ ጠባቂ
ቢኒያም ገነቱ – ወላይታ ድቻ
የጦና ንቦቹ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋሩ የግብ ጠባቂው ብቃት አስደናቂ ነበር። ቢኒያም የቡድን አጋሮቹን በራስ መተማመን ከመጨመሩም ባሻገር 33ኛው እና 57ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ታረቀኝ ከፍጹም ቅጣት ምት የመታቸውን ኳሶችም በመመለስ ቡድኑ ድል ባይቀናውም በግሉ ስኬታማ ቀን ማሳለፍ ችሏል።
ተከላካዮች
ዮናታን ፍስሐ – ፋሲል ከነማ
ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ መድንን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ሁለገቡ የመስመር ተከላካይ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አጨዋወት እየተመቸ የመጣ የሚመስለው እና በመልሶ ማጥቃት ሲጫወት የነበረውን የመድንን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመግታት ረገድ የተሳካ ቀን ያሳለፈው ተጫዋቹ ለማጥቃት ሽግግሩም የራሱን ድርሻ ከመወጣቱ ባለፈ ከግራ መስመር ተከላካይነቱ በተጨማሪ ከዕረፍት መልስ የቦታ ለውጥ በማድረግ ወደ ቀኝ መስመር በመምጣት ጥሩ ግልጋሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህም ዮናታን በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካተት ችሏል።
ኢያሱ ለገሰ – ድሬዳዋ ከተማ
እጅግ ፈጣን የሆኑ አጥቂዎች ባለቤት የሆኑትን ኢትዮጵያ ቡናዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ውስጥ የኢያሱ ለገሰ ድርሻ እጅግ ከፍ ያለ ነበር። በተለይም በሁለቱም የመስመር ማጥቃቶች የሚሻገሩም ሆነ የሚሰነጠቁ ኳሶችን የተቆጣጠረበት መንገድ አስደናቂ ነበር። ተጫዋቹ ከኳስ ውጪ ከነበረው ጠንካራ እንቅስቃሴ ባሻገር በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የነበረው የማሸነፍ ንፃሬ እና ስኬታማ የነበሩት የሚያቋርጣቸው ኳሶች ቡድኑ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ማስቻሉን ተከትሉ ለመጀመርያ ጊዜ በዚህ ዓመት በሳምንቱ ምርጥ ተካቷል።
ተስፋዬ መላኩ – ወልቂጤ ከተማ
ሠራተኞቹ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ግባቸውን ሳያስደፍሩ እንዲወጡ የመሀል ተከላካያቸው ሚና ከፍ ያለ ነበር። በዓየር እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ጥሩ ስኬት የነበረው ተስፋዬ አደገኛ ኳሶችን ከአደጋ ክልል ከማራቅ እና እንቅስቃሴ ከማስጀመር ባለፈ ቡድኑ ከቆሙ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክርም የበኩሉን ጥረት አድርጓል። በዚህም ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ በምርጥ 11 ቡድናችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።
አብዱለጢፍ መሐመድ – ድሬዳዋ ከተማ
ድሬደዋ ከተማ ተከታታይ የሜዳ ላይ ጨዋታውን ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ወሳኝ ድል ባስመዘገበበት ጨዋታ የጋናዊው የመስመር ተከላካይ አብዱለጢፍ መሐመድ አስተዋፆኦ የጎላ ነበር። የኢትዮጵያ ቡናን ፈጣን የመስመር አጨዋወት በመቆጣጠር ረገድ የተሳካ እንቅስቃሴ ያደረገው አብዱለጢፍ ወደፊት ለማጥቃት የሚያደርገው እንቅስቃሴም መልካም የሚባል ከመሆኑ ባሻገር ቻርለስ ሙሴጌ ላስቆጠራቸው ሁለት ግቦችም በማመቻቸት ድንቅ ምሽት ማሳለፉን ተከትሎ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ መካተት ችሏል።
አማካዮች
ሙሉዓለም መስፍን – ወልቂጤ ከተማ
የቀድሞ ክለቡን ሲዳማ ቡና በገጠመበት ጨዋታ አማካዩ ሙሉዓለም ወልቂጤ ከተማ መሀል ሜዳ ላይ ለነበረው አንፃራዊ የበላይነት ቁልፍ ሚና ነበረው። በሽግግሮች ወቅት የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጣ ግብ ላላስተናገደው ለተከላካይ ክፍሉ ከሰጠው ሽፋን በላይም ኳስ በማደራጀት ቡድኑ ከሜዳው እንዲወጣ ያደረገበት አኳኋን ዓይነግቡ ነበር። በዚህም በዚህ ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ በምርጥ አስራ አንድ ስብስብ ውስጥ እንዲካተት ሆኗል።
ዳዊት ተፈራ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
በአስራ ሰባተኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች እንደ ዳዊት ተፈራ ደምቆ የታየ ተጫዋች የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ፈረሰኞቹ ተከታታይ ድል በማስመዝገብ ደረጃቸውን በማሻሻል ወደ መሪዎቹ አናት እንዲጠጉ በማስቻሉ ረገድ የዳዊት ተፈራ ድርሻ እጅጉን ከፍ ያለ ነበር፡፡ ተጫዋቹ የመሐል ሜዳውን በሚገባ ተቆጣጥሮ የማጥቃት ሚዛኑን አስጠብቆ ከመውጣት ባለፈ አንድ በፍፁም ቅጣት ምት አንድ ደግሞ በእንቅስቃሴ በድምሩ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ደምቆ ያመሸ በመሆኑ በምርጥ ስብስብ ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።
ቢኒያም በላይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ፈረሰኞቹ ሀምበርቾን 3ለ1 በረቱበት ጨዋታ እንደ ቡድን አጋሩ ዳዊት ተፈራ ሁሉ ስኬታማ ቀን ያሳለፈው ቢኒያም በላይ ወድድሩ ወደ ትውልድ ከተማው ከሄደ በኋላ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ምቹ በሆነው የድሬዳዋ የመጫወቻ ሜዳ ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ የሚገኝ ሲሆን በተጠቀሰው ጨዋታም አማካዩ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አመቻችቶ ማቀበል ሲችል ሦስተኛውን ግብ ደግሞ በድንቅ ብቃት ማስቆጠር መቻሉ ለተከታታይ ሳምንት በምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።
አጥቂዎች
ተባረክ ሄፋሞ – ሀዋሳ ከተማ
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ በመግባት ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ተባረክ የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል። ኃይቆቹ ባሳለፍነው ሳምንት ሻሸመኔን 3ለ1 ሲያሸንፉ የመስመር አጥቂው ብቃት እጅግ ግሩም ነበር። ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻለው ተባረክ በጨዋታው ጎል አያስቆጥር እንጂ ዓሊ ሱሌይማን እና እስራኤል እሸቱ ላስቆጠሯቸው ግቦችም አመቻችቶ ማቀበል መቻሉ በቦታው ከቢኒያም ዐይተን ጋር ተፎካክሮ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።
ቻርለስ ሙሴጌ – ድሬዳዋ ከተማ
ብርቱካናማዎቹ ኢትዮጵያ ቡና ላይ የ2ለ1 ድል ሲቀዳጁ የዩጋንዳዊው አጥቂ አስተዋጽኦ በጉልህ የሚታይ ነበር። ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቻርለስ ቡድኑ አሸናፊ የሆነባቸውን ሁለት ግቦችንም በስሙ ማስመዝገብ ከመቻሉም ባሻገር በስምንት ጎሎች የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ፉክክር ውስጥ እንዲገባ በመቻሉ በምርጥ 11 ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።
ዓሊ ሱሌይማን – ሀዋሳ ከተማ
እጅግ ፈጣን የሆነው እና በየሳምንቱ ለተከላካዮች ፈታኝ እየሆነ የመጣው ዓሊ ሱሌይማን ቡድኑ ሻሸመኔን 3ለ1 ሲያሸንፍ ያደረገው እንቅስቃሴ እጅግ ማራኪ ነበር። መጠነኛ የአጨራረስ ችግሮች ይኑሩበት እንጂ እንደ ተባረክ ሁሉ ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ በማድረግ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻለው አጥቂው ሁለት ግቦችንም በስሙ ማስመዝገብ ችሏል።
አሰልጣኝ – ኮማንደር ሽመልስ አበበ
ድሬዳዋ ከተማዎች በመቀመጫ ከተማቸው ብርቱ ፉክክር አድርገው ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ1 ሲያሸንፉ በተከታታይ ሳምንታት ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረገ የመጣው የአሰልጣኝ ሽመልስ አበበ የአሸናፊነት ስነልቦና ሚናው ከፍ ያለ ነበር። የማሸነፊያ ቀመሩን እንዳገኙ የገለፁት አሰልጣኙ በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ለተመልካች ሳቢ የሆነ አጨዋወት በመከተል ተከታታይ ድል በማስመዝገብ ቡድናቸው አስደናቂ ግስጋሴ እንዲያደርግ በማስቻላቸው የዚህን ሳምንት ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እና ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ተፎካክረው ሊመረጡ ችለዋል።
ተጠባባቂዎች
ጽዮን መርዕድ – ሀዋሳ ከተማ
ጸጋአብ ዮሐንስ – ሀዋሳ ከተማ
ሳሙኤል ዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና
ሱራፌል ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ
ጋቶች ፓኖም – ፋሲል ከነማ
አፍቅሮተ ሰለሞን – ፋሲል ከነማ
ሀብታሙ ሸዋለም – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ቢኒያም ዐይተን – አዳማ ከተማ
ቸርነት ጉግሳ – ባህር ዳር ከተማ