👉 ግቡን ሳያስደፍር የተጋጣሚ መረብም እምብዛም ሳይደፍር የዘለቀው ሀድያ ሆሳዕና ያለመሸነፍ ጉዞውን አስቀጥሏል።
👉 ያለመሸነፍ ጉዞው የተገታው ወጣት አሰልጣኝ አስደናቂ ጅማሮ
👉 ብርቱካናማዎቹ ድምጻቸውን አጥፍተው ግስጋሴያቸውን እየቀጠሉ ነው።
👉 የሊጉን መልክ የቀየረው የድሬዳዋ ስታዲየም
አስራ ሰባተኛው ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሂደት ከተገማች ውጤቶች እየተላቀቀ ካለፉት የውድድር ዓመታት በተሻለ አጓጊ ሆኗል። ከዚህ ቀደም የጥቂት ክለቦች ፍልሚያ የነበረው ሊጉ በዚ ውድድር ዓመት ግን በርካታ ዋንጫን አልመው ወደ ሜዳ የሚገቡ ክለቦች አግኝቷል። በሊጉ ዙርያ የተለያዩ መረጃዎች የምታቀርብላቹ ሶከር ኢትዮጵያም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያለቻቸውን ጉዳዮች እንደሚከተለው አቅርባለች።
ግቡን ሳያስደፍር የተጋጣሚ መረብም እምብዛም ሳይደፍር የዘለቀው ሀድያ ሆሳዕና ያለመሸነፍ ጉዞውን አስቀጥሏል
በሊጉ ረዥሙን ያለመሸነፍ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች በሁለት ተከታታይ ሳምንታት የገጠማቸውን ፈተና አልፈዋል። ባለፈው ሳምንት የሊጉ መሪ የነበረውን መቻል በማሸነፍ ፤ በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በተመሳሳይ ከመሪው ንግድ ባንክ ጋር አቻ በመለያየት ለአስራ ሦስት ሳምንታት የዘለቀውን ያለመሸነፍ ጉዟቸው አስቀጥለዋል። ቡድኑ ከመቻል ጋር ባደረገው ጨዋታ ምንም እንኳ ከአስራ አምስት ጨዋታዎች በኋላ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ቢያስተናግድም ከሰባት ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥሮ ጣፋጭ ድል ማስመዝገብ ችሏል። ከሊጉ ጠንካራ ቡድኖች አንዱ የሆነው መሪው መቻልን ከማሸነፉ በዘለለ ድሉ ከሁለት ጊዜ መመራት በኋላ የተገኘ መሆኑና ያለመሸነፍ ጉዞውን ያስቀጠለ ወሳኝ ድል እንደመሆኑ ልዩ አድርጎት ነበር። በዚ ሳምንትም በተመሳሳይ በሊጉ ከፍተኛውን የግብ መጠን ያስቆጠረና ድንቅ የፊት መስመር ጥምረት ያለውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገጥሞ የመከላከል አደረጃጀቱ በቀላሉ የማይበገር መሆኑን አስመስክሯል።
ዝቅተኛው የግብ መጠን(11) በማስተናገድ ግቡን ሳያስደፍር፤ በተመሳሳይ ጥቂት ግቦች ካስቆጠሩ ቡድኖች አንዱ በመሆን የተጋጣሚን መረብ እምብዛም ሳይደፍር ያለመሸነፍ ጉዞውን ያስቀጠለው ሀድያ ሆሳዕና ቀጣይ በወራጅ ቀጠናው የሚገኙት ወልቂጤ ከተማ እና ሀምበርቾ ይገጥማል።
ብርቱካናማዎቹ ድምጻቸውን አጥፍተው ግስጋሴያቸውን እያስቀጠሉ ነው
በውጤት ውጣ ውረድ ውስጥ የቆየው የብርቱካናማዎቹ ጉዞ ፈር ከያዘ ሰንበትበት ብሏል። ቡድኑ የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት ሳይቀምስ አራት ድል እና ሁለት የአቻ ውጤት አስመዝግቦ መሻሻሎች አሳይቷል። በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በጥሩ ብቃት ላይ ያለውን ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ኮስታራ ተጋጣሚ መሆኑን አስመስክሯል።
የአሰልጣኝነት መንበሩን በተረከቡ ማግስት ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ስራቸውን የጀመሩት አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ (ኮማንደር) ፈጣን በሚባል ጊዜ ውስጥ ቡድኑን በውጤት ጎዳና እንዲንጎማለል አስችለውታል። ቡድኑ ምንም እንኳ ቀላል የማይባሉ የፊት መስመር ክፍተቶች ቢኖርበትም ከዚ ቀደም በቀላሉ ግቦችን ሲያስተናግድ የነበረው የተከላካይ ክፍል በአዲሱ አሰልጣኝ ስር ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት በጎ ለውጦች አሳይቷል። ብርቱካናማዎቹ በቀጣይ ሳምንታት ከሀዋሳ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ፋሲል ከነማ ከመሳሰሉ ክለቦች የሚገጥማቸውን ፈተና አልፈው ውጤታማነታቸውን ያስቀጥሉ ይሆን? ጊዜ የሚመልሰው ጥያቄ ይሆናል።
ያለመሸነፍ ጉዞው የተገታው ወጣት አሰልጣኝ አስደናቂ ጅማሮ
ቡናማዎቹ ከአምስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሰርቢያዊውን አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪችን አሰናብተው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬን ሲሾሙ ወጣቱ አሰልጣኝ በጊዜያዊነት ይመራል ከሚሉ መላ ምቶች በዘለለ ቡድኑን በዚ መጠን ያሻሽላል ብሎ የገመተ አልነበረም። ወጣቱ አሰልጣኝ ግን እንደ እሳት የሚፋጀውን የቡናማዎቹ የአሰልጣኝነት መንበር ከተቆናጠጠባት ዕለት ጀምሮ ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው እልፍ ለውጦች በማምጣት ያለፉት ዓመታት ቅጥ ያጣው የክለቡ ውጤት ታግሰው ለቆዩ ደጋፊዎች በድል ማጥመቅ ተያይዞታል።
በኢትዮጵያ ዋንጫ ኮልፌ ቀራንዮን በማሸነፍ የጀመረው ወጣቱ አሰልጣኝ መንበሩን ከተረከበ ወዲህ በሁለቱም ውድድሮች ባደረጋቸው አስራ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ተሸንፎ ስምንት ድልና ሦስት የአቻ ውጤቶች ከማስመዝገቡ በዘለለ ሀያ ሦስት ግቦች ያስቆጠረ ስል ቡድን ገንብቷል።
ቡድኑ ምንም እንኳ በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት በብርቱካናማዎቹ የሁለት ለአንድ ሽንፈት ገጥሞት ያለመሸነፍ ግስጋሴው ቢገታም የቡድኑ እንቅስቃሴ እና ስር ነቀል ለውጥ ያመጣው የአሰልጣኙን አብዮት አለማድነቅ ከቶ አይቻልም።
የሊጉን መልክ የቀየረው የድሬዳዋ ስታድየም
በአዲስ መልክ ታድሶ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የጀመረው የድሬዳዋ ስቴድየም በሊጉ ታሪክ በብዙ መመዘኛዎች የተሻለ እንደሆነ መስካሪ የማያስፈልገው እውነታ ነው። ለጨዋታ ምቹ የሆነ የመጫወቻ ሜዳና ካለ ምንም ችግር የምሽት ጨዋታዎች ማስተናገድ የሚችል መብራት የተገጠመለት ይህ ስቴድየም ለሊጉ ራሱን የቻለ ድምቀት ጨምሯል። ከዚህ በተጨማሪ በሜዳ ጥራት ችግር መነሻነት ለሚገጥሙ ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት ይቀንሳል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ስቴድየም በዝናባማ ወቅትም ጥራቱ ሳይዛነፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደሚችል አረጋግጧል። ከዚህ ባለፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ በስታዲየሞች ቁጥራቸው ተመናምነው የነበሩት ደጋፊዎች ሊጉ ወደ ድሬዳዋ ካቀና በኋላ በአንጻራዊነት በተሻለ በክለባቸው ትጥቆች ተውበው ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሰዋል።