በአስራ ስምንተኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚደረጉ ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
በሂደት ወደ ጥሩ አቋም የመጡትና በሦስት ነጥብ የሚለያዩ ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች
በሀያ አምስት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት ጥሩ መሻሻል ካሳዩ ቡድኖች ይጠቀሳሉ። ብርቱካናማዎቹ ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አልቀመሱም፤ በአራቱ ድል በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግም ነጥብ ተካፍለው በመውጣት በተጠቀሱት ሳምንታት ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች አስራ አራቱን አሳክተዋል። ይህም የቡድኑን መሻሻል አንድ ማሳያ ነው። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ድሎች ከማስመዝገቡም ባለፈ በመጨረሻው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ ወደዚ ጨዋታ የሚቀርብ እንደመሆኑ ቀላል ግምት እንዳይሰጠው ያደርጋል። ቡድኑን በዋና አሰልጣኝንት መምራት ከጀመሩ ወዲህ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ መረቡን ያላስደፈረ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል መገንባት የቻሉት አሰልጣኝ ሽመልስ በቀለ(ኮማንደር) በነገው ዕለት በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙ አጥቂዎች ያሉበት ቡድን እንደመግጠማቸው የተከላካይ ክፍላቸው መፈተኑ አይቀሪ ነው።
ከተከታታይ አምስት ሽንፈቶች ወዲህ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ጥሩ መሻሻል ያሳዩት ሀዋሳ ከተማዎች በመሀል ከገጠሟቸው ሁለት ሽንፈቶች ውጭ በውጤት ረገድ መሻሻሎች አሳይተዋል። ሀዋሳዎች ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ከሚመርጡ የሊጉ ቡድኖች ይጠቀሳሉ፤ በሂደት ውጤታማ የሆነውና በፈጣን አጥቂዎች ላይ መሰረት ያደረገው አጨዋወትም የቡድኑ ዋነኛው ጠንካራ ጎን ነው። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ማስቆጠር የቻሉት ሀይቆቹ በነገው ዕለት የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል ይሆናል ተብሎ አይገመትም። በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ የሀዋሳ ከተማ አጥቂዎች ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ካስተናገደው የብርቱካናማዎቹ የተከላካይ መስመር የሚያደርጉት ፍልምያም የጨዋታውን ውጤት ከሚወስኑ ሂደቶች አንዱ ነው።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ተመስገን ደረስና አብዱልፈታህ ዓሊ በጉዳት፤ ኤልያስ አህመድና አቤል አሰበ ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ ተሳትፎ አይኖራቸውም። በቤተሰብ ችግር ከቡድኑ ጋር የሌለው ዳዊት እስቲፋኖስም በነገው ጨዋታ አይኖርም። በሀዋሳ ከተማዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ክለቦች ነገ በሊጉ ለ24ኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች 8 ፣ ድሬዳዋ ከተማዎች 6 ድል አስመዝግበው በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ሀይቆቹ 25 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ብርቱካናማዎቹ ደግሞ 22 ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።
መቻል ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች
ሊጉን በሁለት ነጥብ ልዩነት በመምራት ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ላይ አቻ ተለያይተው ልዩነቱን የሚያሰፉበት ወርቃማ ዕድል ቢያባክኑም ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ወደ ጥሩ ብቃት መምጣት ችለዋል። ቡድኑ ፋሲል ከነማ ከነማና አዳማ ከተማን ማሸነፉ እንዲሁም በረዥም ያለመሸነፍ ጉዞ ላይ ካለው ሀድያ ሆሳዕና ባደረገው ጨዋታ ነጥብ ተካፍሎ መውጣቱ ከመጥፎው የሁለት ጨዋታዎች አቋም ቶሎ አገግሞ ወደ ጥሩ ብቃት መምጣቱ ማሳያ ናቸው። ባንኮች ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ስምንት ግቦች ማስቆጠር ችለው ነበር። ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ባደረጉትና ባዶ ለባዶ በተጠናቀቀው ጨዋታ ግን የተሻለ የኳስ ቁጥጥር መያዝ ቢችሉም ብልጫውን ተጠቅመው በዛ ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። በነገው ጨዋታ ምንም እንኳ ጠንከር ያለ የመከላከል ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም ከጨዋታውን ክብደትና ከውጤቱ አስፈላጊነት አንፃር ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስተናገደው መቻል በነገው ጨዋታ ተመሳሳይ ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ይኖረዋል ተብሎ አይታመንም። ስለዚህም ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጨረሻው ጨዋታ በሦስተኛ የሜዳ ክፍል የነበራቸውን ክፍተቶች ማረም ግድ ይላቸዋል። ከዚ በዘለለ ከነብሮቹ ጋር በተደረገ ጨዋታ የተጋጣሚን ሽግግሮች የመግታት ውስን ክፍተት የታየበት የተከላካይ ክፍል በነገው ዕለትም ሽግግርን በተሻለ መንገድ ሊያሳኩ የሚችሉ ተጫዋቾች ካሉበት መቻል መሰል ፈተናዎች ማስተናገዱ አይቀሪ ነው።
ጨዋታው በዋንጫ ፉክክሩ ነጥብ ቀያሪና ወሳኝ እንደመሆኑ የሜዳ ላይ ፉክክሩ ቀላል አይሆንም።
ሁለት ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደው መሪነታቸውን የተነጠቁት መቻሎች በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ከዚ ጨዋታ ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። መቻሎች ለተከታታይ አስራ አንድ ጨዋታዎች ከዘለቀው ያለመሸነፍ ጉዞ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈትና አንድ ድል ማስመዝገብ ችለዋል። ሁለተኛውን ዙር ከተጀመረ ወዲህ ሦስት ነጥብ ማሳካት ያልቻሉት መቻሎች ምንም እንኳ ተከታታይ ሽንፈቶች ቢያስተናግዱም እንቅስቃሴያቸው መጥፎ አልነበረም። ሆኖም ብልጫን ወደ ውጤት የመቀየር እና ጉልህ የመከላከል ድክመቶች ይታይባቸዋል። በተለይም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ክፍተቶቹን ማረም ይጠበቅበታል፤ ቡድኑ በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 1.8 ግቦች ያስቆጠረ ስል የፊት መስመር ያለው ቡድን ስለሚገጥም በሁሉም ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ግድ ይለዋል። የመቻል የመከላከል አደረጃጀት ከጠንካራው የባንክ የፊት መስመር የሚያደርጉት ፍልምያም የጨዋታውን ውጤት ከሚወስኑ ሂደቶች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ጉዳት ላይ ያለው ብሩክ እንዳለ ባለማገገሙ አይሰለፍም ከዚ በተጨማሪ በልምምድ መጠነኛ ጉዳት የደረሰው ፉዓድ ፈረጃ በወሳኙ ጨዋታ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በመቻል በኩል የመሃል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ በአምስት ቢጫ ካርዶች ምክንያት በነገው ጨዋታ አይኖርም።
ሁለቱ በሊጉ ለ26 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን መቻል 8 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ባንክ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 13 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 35 ሲያስቆጥር ባንክ 31 አስቆጥሯል።