በምሽቱ መርሐግብር አዳማዎች ከፍጹም የጨዋታ ብልጫ ጋር ሀምበርቾን 3ለ0 ረተዋል።
በምሽቱ ጨዋታ ሀምበርቾ እና አዳማ ከተማ ሲገናኙ ሀምበርቾዎች በ17ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 3ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ትዕግስቱ አበራ ፣ አቤል ዘውዱ እና በፍቃዱ አስረሳኸኝ ወጥተው ታዬ ወርቁ እና ከቀናት በፊት ቡድኑን የተቀላቀሉት ብርሃኑ አሻሞ እና በኃይሉ ተሻገር ተተክተዋል። ከወላይታ ድቻ ጋር 1ለ1 ተለያይተው የመጡት አዳማ ከተማዎች ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ በቀይ ካርድ ከሜዳ በወጣው አድናን ረሻድ ምትክ ሙሴ ኪሮስን ወደ ቋሚ አሰላለፍ አካተዋል።
1 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ አዳማዎች መጠነኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሁለቱም ፈታኝ አልነበሩም። ሆኖም ግን 12ኛው ደቂቃ ላይ ጀሚል ያዕቆብ ከቀኝ ወደ ውስጥ ቀንሶት ቦና ዓሊ በቄንጥ ለማግባት ሞክሮ ያላገኘው እንዲሁም 17ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ከቀኝ ወደ ውስጥ ቀንሶት ቦና ዓሊ ያደረገው ኃይል የለሽ ሙከራ በአዳማ በኩል ተጠቃሽ ነበሩ።
በቁጥር እየበዙ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መታተራቸውን የቀጠሉት አዳማዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ቦና ዓሊ በግሩም ዕይታ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ አንድ ተከላካይ አልፎ በግራ እግሩ በኃይል የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በደቂቃዎች ልዩነትም ዮሴፍ ታረቀኝ እና ቦና ዓሊ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።
ጨዋታው 41ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዳማዎች ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ታየ ጋሻው ከረጅም ርቀት ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ ዲንክ ኪያር በግንባሩ ለመግጨት ሲሞክር ተደርቦ የመለሰው ቦና ዓሊ ሁለት ጊዜ ገፍቶ በማመቻቸት በግሩም አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት እና የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እጅግ የተቸገሩት ሀምበርቾዎች 45ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን አድርገዋል። ብርሃኑ አሻሞ ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት አስደናቂ በሆነ ሁኔታ አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ አስወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስ ሀምበርቾዎች ጨዋታውን በተሻለ ግለት ቢጀምሩም 51ኛው ደቂቃ ላይ ልፋታቸው ላይ ውሃ የሚቸልስ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ዮሴፍ ታረቀኝ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ከመስዑድ መሐመድ የተቀበለው ኳስ ወደፊት ሲገፋ ታየ ወርቁ ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ቦና ዓሊ በተረጋጋ ሁኔታ በግራ በኩል ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፓጁ በማይደረስበት ርቀት ከፍ አድርጎ በመምታት አስቆጥሮታል።
አዳማዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር ተረጋግተው ማስቀጠል ሲችሉ 56ኛው ደቂቃ ላይም በሳዲቅ ዳሪ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት የወጣች ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ሀምበርቾዎች የተጫዋቾች ቅያሪ ቢያደርጉም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲቸገሩ 70ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ፍቅሩ ዓለማየሁ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ባስገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፓጁ መልሶበታል።
የአዳማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ብቻ እየታየበት እና ፉክክሩ ይበልጥ እየተቀዛቀዘ በቀጠለበት ጨዋታ አዳማዎች 76ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ፍቅሩ ዓለማየሁ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ ተከላካዮችን አታልሎ ኳሱን በማመቻቸት እና መሬት ለመሬት በመምታት የግቡን የግራ ቋሚ የገጨች ግብ አስቆጥሯል። በቀሪ ደቂቃዎችም የአዳማው አህመድ ረሺድ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፓጁ ከመለሰበት እና 90+4ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የሀምበርቾው በፍቃዱ አስረሳኸኝ በግንባር ገጭቶት ከወጣበት ኳስ የተሻለ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሀምበርቾዎች ገና በ18ኛ ሳምንት 13ኛ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበርቾው ምክትል አሰልጣኝ መላኩ ከበደ በየ ጨዋታው ስህተቶቻቸውን ማስተካከል እንዳልቻሉ በመናገር ተጫዋቾች በስነልቦና ችግር ላይ በመሆናቸው ክለቡ ከተጫዋቾቹ ጋር ተነጋግሮ ችግሮቹን እንዲፈታ አጥብቀው በመጠየቅ ባለመውረድ ትንቅንቁ ተስፋ እንደማይቆርጡም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ጨዋታውን እንደጠበቁት እስከ 40 ደቂቃ ጠንካራ እንደነበር እና ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ክፍት እንደሆነላቸው በመናገር ቦና ዓሊ ፍጹም ቅጣት ምቱን የመታው ከዮሴፍ ጋር ተነጋግሮ እንደሆነ በመጠቆም የቦና ዓሊን እንቅስቃሴም እያደገ እንደመጣ እና ያም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።