የሊጉን መሪዎች ባገናኘው የምሽቱ ጨዋታ መቻል ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2ለ0 በመርታት ወደ ሊጉ አናት ብቅ ብሏል።
ሁለቱ ቡድኖች ከባለፈው የጨዋታ ሳምንታቸው በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀድያ ሆሳዕናው ጨዋታ ባደረጉት ለውጥ ካሌብ አማንኩዋ እና አዲስ ግደይን በእንዳለ ዮሐንስ እና ፉዓድ ፈረጃ በባህርዳር ሽንፈት ገጥሟቸው የነበሩት መቻሎች በበኩላቸው አስቻለው ታመነን በስቴፈን ባዱ አኖርኬ ፣ ፍፁም አለሙን በዮሐንስ መንግስቱ ተክተዋቸዋል።
የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ጎሎችን ያስመለከተን ገና በጊዜ ነበር። ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጨዋታውን የጀመሩት መቻሎች 3ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሆነዋል። ከነዓን ማርክነህ ከቀኝ በጥሩ የእግር ስራ ወደ ውስጥ የሰጠውን በሐይሉ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ምንይሉ ወንደሙ መረቡ ላይ አሳርፏታል። የንግድ ባንክን ያልተደራጀ መከላከል በድግግሞሽ ወደ ቀኝ በማዘንበል ከሽመልስ በሚነሱ ስርጭቶች በከነዓን እና ግሩም ጥሩ ጥምረቶች ጫና ማሳደርን የቀጠሉት መቻሎች ከሦስት ደቂቃ በኋላም ተጨማሪ ጎል ወደ ካዝናቸው ከተዋል። ከበሐይሉ መነሻዋን ያደረገችን ኳስ ዮሐንስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ መቷት ፍሬው ሲመልሳት አቤል ነጋሽ አግኝቶ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል። የተጋጣሚያቸውን የመስመር እና ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ተንጠልጣይ ኳሶችን ለመቋቋም የከበዳቸው ንግድ ባንኮች 23ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። ከቀኝ ምንይሉ የሰጠውን ከነዓን ሞክሮ ለጥቂት ወጥባታለች።
ከወትሮ ወረድ ብለው ሲንቀሳቀሱ የታዩት ንግድ ባንኮች ካዘወተሩት የኋሊዮሽ ቅብብል መለስ በማለት ወደ ሽግግር አጨዋወት ከገቡ በኋላ 30ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራን አድርገዋል። ባሲሩ በጥሩ ዕይታ ያቀበለውን ቢኒያም በግራ እግሩ በቀጥታ መቶ አሊዮንዚ ያዳነበት በአጋማሹ ጠጣሯ ሙከራቸው ሆናለች። ንግድ ባንኮች እንዳለ ዮሐንስን በካሌብ አማንክዋ ፣ አዲስ ግደይን በሀብታሙ ሸዋለም በመተካት ወደ ጨዋታ ሪትም ለመግባት ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም መቻሎች በቀኝ ኮሪደር በኩል ሲያጠቁ የነበራቸውን ግለት መቆጣጠር ተስኗቸው ተስተውሏል። ለዚህም ሌላ ማሳያ ከነዓን ሦስተኛ ግብ የምትሆን አጋጣሚን ፈጥሮ ፍሬው አምክኖበት አጋማሹም በ2ለ0 የመቻል መሪነት ተጋምሷል።
ከዕረፍት ጨዋታው እንደተመለሠ ባሉት አምስት ያህል ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከጎል ጋር ለመገናኘት በተሻጋሪ ኳሶችን ብልጫውን ለመያዝ ጥቂት ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም የመቻልን ጥቅጥቅ ያለ መከላከል አልፈው ግብን ለማግኘት ግን በእጅጉ ሲቸገሩ ማየት ችለናል። 58ኛው ደቂቃ የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገዱ ንግድ ባንክ ከቆመ የቅጣት ምት ኳስ በፉዓድ ፈረጃ አማካኝነት ጥሩ አጋጣሚን ፈጥረው ግብ ጠባቂው አሊዮንዚ ናፊያን የተደረገችዋን አደገኛ ሙከራ አውጥቷታል። ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ ሜዳውን በመለጠጥ ቀስ በቀስ ጨዋታውን መቆጣጠር የጀመሩት መቻሎች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ቶሎ ቶሎ የደረሱበትን አጋጣሚ በሂደት ማየት ብንችልም በቀላሉ የሚያገኟቸውን ግልፅ ዕድሎች በተደጋጋሚ በሚታይባቸው ዝንጉነት ሲያመክኑ ተስተውሏል።
ንግድ ባንኮች 71ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ በረከት ግዛውን በአጥቂው ሲሞን ፒተር በመተካት የፊት መስመር ቁጥራቸውን ከፍ ቢያደርጉም ልዩነት ለመፍጠር በሚሄዱበት ወቅት ግን ስልነት አብሯቸው አልነበረም። በሙከራዎች ረገድ ደብዝዞ በቀጠለው ቀጣዮቹ የጨዋታ ደቂቃዎች የተሻለውን ሙከራ 76ኛው ደቂቃ ላይ በመቻል በኩል ያስተዋልን ሲሆን ምንይሉ ከቀኝ የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን እየነዳ ገብቶ በቀላሉ አስቆጠረው ሲባል ፍሬው ጌታሁን በንቃት ያዳነበት ተጠቃሿ ሙከራ ነበረች። በጨዋታው የጭማሪ ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች ከቆመ ኳስ አዲስ ግደይ ባደረጋት ዒላማውን ያልጠበቀች የቅጣት ምት እና ቢኒያም ጌታቸው አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ከተባለች አጋጣሚ በኋላ ጨዋታው በመጨረሻም ጨዋታው በመቻል የ2ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ አጀማመራችን መጥፎ በመሆኑ በሰባት ደቂቃ ውስጥ የተቆጠሩ ድንገተኛ ጎሎች ወደ ጨዋታ እንዳይመለሱ እንዳደረጋቸው ጠቁመው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት አድርገው በተጋጣሚያቸው መቀደማቸው ውጤት ይዘው እንዳይወጡ እክል እንደሆነባቸው ተናግረዋል። የመቻሉ ረዳት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ በበኩላቸው በስልቦና ቡድኑ ከፍ ያለ ስሜት ስለነበረው መነቃቃቶችም ሜዳ ላይ መታየት መቻላቸው የተገኙ ዕድሎችን በመጠቀም ድልን ማግኘት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።