በምድብ “ለ” የሁለተኛ ዙር የሁለተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በተደረጉ ጨዋታዎች የካ ክ/ከተማ እና ደብረ ብርሀን ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ረፋድ 5:00 ላይ የተደረገው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የካ ክ/ከተማ ቢሾፍቱ ከተማን አሸንፏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ በመቆጣጠር እና በፍጥነት ወደ ግብ በመድረስ ቢሾፍቱ ከተማ ተሽለው የተገኙት አጋማሽ ሆኗል። በአንፃሩ የካ ክ/ከተማ የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በ24ኛው ደቂቃ የቢሾፍቱ ከተማ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው አብዱልአዚዝ ኡመር ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ የየካ ክ/ከተማ ግብ ጠባቂ ወደ ውጪ አውጥጦታል።
ጨዋታው በዚህ እንቅስቃሴ ቆይቶ መደበኛው የጨዋታው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ የካ ክ/ከተማ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በመሄድ ጁኔክስ አወቀ ወደ ግብ ሲመታው የቢሾፍቱ ተከላካይ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ጁኔክስ አወቀ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ቢሾፍቱ ከተማ የተወሰደበትን የግብ ብልጫ ለመቀልበስ ኳስን በመቆጣጠር ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ የካ ክ/ከተማ የወሰደውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ በጥሩ ሁኔታ በመከላከል የሚያገኙትን ኳስ በፈጣን ሽግግር የግብ እድል ለመፍጠር ሞክረዋል። በ67ኛው ደቂቃ ቢሾፍቱ ከተማ የየካ ክ/ከተማ የግብ ክልል አግኝተው ወደ ግብ የሞከሩትን ኳስ የካ ክ/ከተማ በመቆጣጠር በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ቢሾፍቱ የግብ ክልል በመሄድ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ጁኔክስ አወቀ በቀላሉ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የካ ክ/ከተማ የተጫዋች ቅያሪ አድርገው ጥንቃቄ በመጨመር ምንም ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታው 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በመቀጠል 7:00 ላይ በተደረገው መርሀግብር ደብረ ብርሀን ከተማ ነጌሌ አርሲን 1-0 አሸንፏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እና ከፍተኛ የሆነ ፉክክር የታየበት አጨዋወትን ተመልክተናል። ነጌሌ አርሲ ኳስ ቁጥጥሩም ጥሩ የሚባል እና በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመሄድ የግብ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በ34ኛው ደቂቃ ላይ የአርሲ ተጫዋች የሆነው ገብረ መስቀል ዱባለ በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶት ወደ ውጪ ወጥቷል። አጋማሹም ምንም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ደብረ ብርሀን ከተማ ተነቃቅተው እና በጥሩ መንፈስ የገቡ ሲሆን በአንፃሩ ነጌሌ አርሲዎች ተቀዛቅዘው ታይተዋል። በ68ኛው ደቂቃ ደብረ ብርሀን ከተማ ከጥልቀት ተነስተው በፈጣን ቅብብል በመሸጋገር ልደቱ ጌታቸው ከአርሲ ነጌሌ የግብ ክልል ውጪ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ብዙም ሳይቆይ በነጌሌ አርሲ በኩል ተቀይሮ የገባው ፍቅሩ ጴጥሮስ በፈፀመው ጥፋት የእለቱ የመሀል ዳኛ በስህተት ለምንተስኖት ተስፋዬ የቀይ ካርድ በማሳየታቸው ከፍተኛ የሆነ አለመግባባት ተፈጥሮ ጨዋታው ለደቂቃዎች መቋረጡ ተስተውሏል። የቀረውን ደቂቃ አርሲ ነጌሌ የተጫዋች ብልጫ ተወስዶባቸውም ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ጨዋታው በደብረ ብርሀን ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።