መረጃዎች| 73ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ 18ኛ ሳምንት ማሳረጊያ በሆኑት ሁለት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አሰናድተናል።

ፋሲል ከነማ ከ ሲዳማ ቡና

የነጥብ ልዩነቱ ለማጥበብ ወደ ሜዳ የሚገው ፋሲል ከነማና ከድል ለመታረቅ የሚያልመው ሲዳማ ቡና የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ወጥነት ከጎደለው የአምስት ሳምንታት ብቃት አገግመው ሁለት ተከታታይ ድሎች ያስመዘገቡት ዐፄዎቹ ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን ልዩነት የሚያጠቡበት ዕድል አግኝተዋል። ቀደም ብለው ጨዋታቸው ያደረጉት በሊጉ አናት ያሉት ቡድኖች ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ዐፄዎቹ ወደ ፉክክሩ ብቅ የሚሉበት ቀዳዳ አግኝተዋል። ይህንን ተከትሎም ቡድኑ በተሻለ አዕምሯዊ ከፍታ ሆኖ ወደ ሜዳ የሚገባበት ዕድል የሰፋ ነው። ቡድኑ ከቅርብ ሳምንታት በፊት ከኳስ ቁጥጥር ባለፈ በሚታወቅበት አኳኋን በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ክፍተቶችን ፈልጎ በማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን የሚያደርግበት እንቅስቃሴም አብሮት አልነበረም። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግን በመጨረሻው የሜዳ ክፍል ያለውን አፈፃፀም አሻሽሎ ቀርቧል፤ ቡድኑ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጥሩም የዚ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም የፊት መስመሩ ፍሬአማነት ቀጣይ መሆን እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።

19 ነጥቦች ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ከተከታታይ ድሎቹ በኋላ በጣላቸው ነጥቦች ደረጃው አሽቆልቁሏል። በወራጅ ቀጠናው ካለው ቡድን የስድስት ነጥብ ልዩነት ያለው ቡድኑ ስጋት ውስጥ ይገኛል ለማለት ባይቻልም የነጥብ ስብስቡን ከፍ አድርጎ ሙሉ ለሙሉ ራሱን ነፃ ማድረግ እንደሚኖርበት አይካድም። ሲዳማ ቡናዎች ከተከታታይ ሽንፈቶቹ በዘለለ አሁንም ወጥ ግብ አስቆጣሪ ያለማግኘታቸው ጉዳይ እንደፈተናቸው ማንሳት ይቻላል። ቡድኑ ንግድ ባንክን ሁለት ለአንድ ካሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ላይ ግብ አለማስቆጠሩ ሲታይ የተጠቀሰው ክፍተት የቡድኑ ዋነኛ ችግር እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በነገው ጨዋታም ከሊጉ ጠንካራ የመከላከል ጥምረቶች አንዱ እንደመግጠሙ የሚጠብቀው ፈተና በብቃት መወጣት የሚችል የፊት መስመር ጥምረት ያስፈልገዋል።

በዐፄዎቹ በኩል ዓለምብርሃን ይግዛው እና አፍቅሮተ ሰለሞን በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። ሲዳማ ቡናዎች ግን በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

13 ጊዜ በሊጉ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ሁሉንም በመሸናነፍ ያጠናቀቁ ሲሆን ፋሲል 8 ፣ ሲዳማ ቡና 5 ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል። ፋሲል ከነማ 20 ግቦች ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና ደግሞ 14 አስቆጥሯል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)


ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ መድን

በአስር ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኛው የሳምንቱ መገባደጃ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

በቅርብ ሳምንታት ወዲህ ባስመዘገቧቸው ደካማ ውጤቶች ደረጃቸው ያሽቆለቆለው ወላይታ ድቻዎች ድል ካደረጉ አራት ሳምንታት ተቆጥረዋል። ቡድኑ በአብዛኛውን ጊዜው በሰንጠረዡ ከወገብ በላይ ሆኖ ቢዘልቅም የቅርብ ሳምንታት ውጤቱ ግን ደረጃውን አውርዶታል። በነገው ጨዋታም በተከታታይ ነጥብ ላለመጣልና ደረጃውን ለማሻሻል አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይታመናል። የጦና ንቦቹ የግብ ማስቆጠር ችግራቸው ቀጥሏል። በመጨረሻዎቹ ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው ቡድኑ ወሳኙ አጥቂው ቢንያም ፍቅሩ በቅጣት በማጣቱ ችግሩ እንዳያባብሰው ከወዲሁ ሁነኛ ተተኪ ማበጀት ይኖርበታል።

ደካማው የመጀመርያው ዙር ውጤታቸው ለመቀልበስ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ያዘዋወሩት መድኖች ከባለፉት ሳምንታት የተሻለ ጥልቀት ያለው ቡድን ይዘው ይቀርባሉ። ዘጠኝ ድል ኣልባ ሳምንታት ያሳለፉት መድኖች ከስጋት ቀጠናው ለመላቀቅ ከወዲሁ ነጥቦች መሰብሰብ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ የተሻለ ተንቀሳቅሶ ሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤት ካስመዘገበ በኋላ በፋሲል ከነማ ሽንፈት ቢገጥመውም ቡድኑ አንድ ደረጃ ሊያሻሽሉ የሚችሉ በርከት ያሉ ዝውውሮች እንደመፈፀሙ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ላይ ለውጦች ሊኖር የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው። በተለይም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግብ ሳያስቆጥር የወጣው የቡድኑ የፊት መስመር ስር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልገው ክፍል ነው።

ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ተገናኝተው ድቻ 2 ሲያሸነፍ መድን አንድ አሸንፎ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ድቻ 6፣ መድን 3 ግቦች በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።