በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው መቻል ከናይጀሪያዊው አጥቂ ጋር በመለያየት በምትኩ ቶጓዊ አጥቂ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።
በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው መቻል በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን በ18 ሳምንታት የሊጉ ጨዋታዎች 36 ነጥቦችን በመሰብሰብ 3ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ክለቡ አሁን በሚገኝበት የዋንጫ ፉክክር ለመዝለቅ የውድድር አጋማሽ የዝውውር መስኮት ማገባደጃ ዕለት የአጥቂ መስመር ተጫዋች ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ክለቡ አዲሱን ተጫዋች ከማስፈረሙ በፊት ክረምት ላይ ወደ ስብስቡ ከቀላቀለው ናይጄሪያዊ አጥቂ ቺጂኦኬ አኩኔቶ ጋር ያለውን ውል በስምምነት በዛሬው ዕለት አቋርጧል። በምትኩም የቶጎ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነውን አብዱ ሙታላቡ ኡታራን አስፈርሟል።
አንድ ሜትር ከሰባ ሁለት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው የመሐል አጥቂ በሀገሩ ክለብ አስኮ ካራ እና በቡርኪና ፋሶው ሶናብል ከ2018 ጀምሮ ቆይታ ያደረገ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ደግሞ ወደ ሳውዲ በማምራት በአል-ናይሪያ ክለብ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። ተጫዋቹ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ዛሬ በይፋ ለመቻል የአንድ ዓመት ውል ፈርሟል።
ተጫዋቹ በዚሁ ከቡድኑ ጋር ዝግጅቱን እንዲያደርግ ቢፈለግም ቶጎ ከኒጀር እና ሊቢያ ጋር ላለባት ጨዋታ ጥሪ ስለተደረገለት ዳግም ወደ ሀገሩ አምርቶ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በኋላ ከቡድኑ ጋር ልምምድ እንደሚጀምር ተገልጿል።