የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ “ሀ” 15ኛ የጨዋታ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲገባደድ የምድብ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ሲጥል ሀላባ ከተማ ድል አስመዝግቧል።
ረፋድ 3 ሰዓት ላይ በተከናወነው የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከነቀምቴ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቷል።
ጥሩ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን አድርገዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የነበረ የኳስ ቁጥጥር የተመለከትንበት ሲሆን በዚህም ኤሌክትሪኮች ኳስን ከኃላ መስርተው ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ነቀምቴዎች ደግሞ ይበልጥ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል።
በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች ለተመልካች ለማሳየት በተቸገረው ጨዋታው አጋማሹ ያለ ግብ ነበር ፍፃሜውን ያገኘው።
ከመልበሻ ክፍል መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጠንከር ብለው የተመለሱ ሲሆን በዚህም ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል በዚህም በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።
ነቀምቴዎች በአንፃሩ የአቻውን ውጤት አስፈላጊነት በመረዳት ወደኋላ አፈግፍገው በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውለዋል።በዚህም አጋማሹ በኤሌክትሪክ ብልጫ የተከወነ ነበር።
ኤሌክትሪኮች መድረሻቸውን አቤል ሀብታሙ ባደረጉ ኳሶችን ዕድሎችን ለመፍጠር ታትረዋል። ለአብነትም በ46ኛው ደቂቃ አቤል ሀብታሙ ከመስመር የተሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለትንሽ በግብ አግዳም በኩል የወጣችበት እንዲሁም በ49ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኩ ያሬድ ብርሃኑ በመስመር በኩል ሆኖ ወደግብ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
ነገርግን ኤሌክትሪኮች በሁለቱም አጋማሾች የነበራቸውን የበላይነት በግብ መመንዘር ሳይችሉ ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል ይህም ኤሌክትሪኮች በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው እንዲፈፅሙ አስገድዷል።
የሳምንቱ ማሳረጊያ የነበረው መርሃግብር በሀላባ ከተማ እና በጅማ አባ ቡና መካከል የተደረገ ሲሆን ጨዋታውም በሀላባ ከተማ አሸናፊነት ተፈፅሟል።
በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ደካማ እንቅስቃሴን ያደረጉበት ሲሆን ሀላባ ከተማዎች ግን አንፃራዊ የበላይነት ነበራቸው።
ሀላባ ከተማዎች ኳስን መስርተው ከተከላካይ መስመር ወደፊት ይዘው መግባት ቢችሉም በመጀመሪያ አጋማሽ ጠንካራ ሆኖ የተገኘውን የጅማ አባ ቡና ተከላካይ መስመር አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል።ጅማ አባ ቡናዎች በአንፃሩ በመጀመሪያ አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ እንቅሰቃሴ አስመልክተዋል።በዚህም የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ሳያስመለከተን ተጠናቋል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ ሀላባ ከተማ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ ማግባት ሙከራዎችንም እንዲሁ ደጋግመው አድርገዋል።በ51ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ከማል ሀጂ በእራሱ ጥረት ኳስን ይዞ በመግባት ከመረብ ጋር ባገናኛት ኳስ ሀላባ ከተማን መሪ እንዲሆኑ አስችሏል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በርበሬዎች ወደኋላ በመመለስ በመከላከል የተጫወቱ ሲሆን ጅማ አባ ቡናዎች ደግሞ በተቃራኒው ወደፊት ኳስን ይዘው በመግባት የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና ለመፍጠር ጥረዋል።
ጅማ አባ ቡና በብዙ መስፈርቶች ብልጫን ይዘው በተጫወቱበት በሁለተኛ አጋማሽ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ቢችሉ ኖር ነጥብ ተጋርተው መውጣት በቻሉ ነበር።ሆኖም ግን አጨራረሳቸውን ማሳመር ባለመቻላቸወሰ ጨዋታው በሀላባ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።