ሪፖርት | ዐፄዎቹ ወደ መሪዎቹ ሊጠጉበት የሚችሉበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል

አራት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና አቻ ተለያይተዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና ሲገናኙ ዐፄዎቹ በ17ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን 2ለ0 ሲያሸንፉ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ሲዳማዎች በአንጻሩ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለ ግብ ከተለያዩበት አሰላለፋቸው አንተነህ ተስፋዬ ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና ሀብታሙ ገዛኸኝን አስወጥተው ደስታ ዮሐንስ ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና ይገዙ ቦጋለን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል።

10፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሲዳማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን በመውሰድ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። 4ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ በቀለ ከቀኝ መስመር ባሻማው ኳስ ማይክል ኪፖሩል በግንባር በመግጨት 12ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ይገዙ ቦጋለ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችም ተጠቃሽ ናቸው።

ከውሃ ዕረፍት በኋላ በመጠኑ ተሻሽለው የቀጠሉት ፋሲል ከነማዎች 29ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድል ፈጥረው ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጋቶች ፓኖም ዒላማውን ባልጠበቀ የጭንቅላት ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ጨዋታው 43ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሲዳማዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ኳስ በእግሩ ለመቆጣጠር ሲሞክር በሠራው ስህተት ኳሱን ያገኘው ማይክል ኪፖሩል በቀላሉ አስቆጥሮታል። ሆኖም መሪነታቸው የዘለቀው ግን ለሦስት ደቂቃዎች ያህል ብቻ ነበር። አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ አቤል እንዳለ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥን አጠገብ በድንቅ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል በጥሩ ግለት የጀመሩት ዐፄዎቹ በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው በግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ሲመለስባቸው 48ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ጌታነህ ከበደ ከኤልያስ ማሞ በተቀበለው ኳስ ወርቃማ የግብ ዕድል ቢያገኝም ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በድጋሚ ይዞበታል።

በሁለቱም በኩል ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ሲዳማዎች 51ኛው እና 58ኛው ደቂቃ ላይ በይገዙ ቦጋለ 55ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በቡልቻ ሹራ አማካኝነት ያደረጓቸው ሦስት ሙከራዎችን በግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ሲመለሱ ፋሲሎች በአንጻሩ 61ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ቃልኪዳን ዘላለም ከአቤል እንዳለ በተሰነጠቀለት ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው 64ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ፋሲል ከነማዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁን ተቀይሮ በገባበት ቅጽበት በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ሆኖም በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ሲዳማዎች ፈጣን ምላሽ ሰጥተው ግብ አስቆጥረዋል። ማይክል ኪፖሩል ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ኢዮብ ማቲያስን በማለፍ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ የግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ስህተት ተጨምሮበት ግብ ሆኗል።

መጠነኛ ፉክክር እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ ፋሲሎች 79ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበት ንጹህ የግብ ዕድል አግኝተው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት በመምታት ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ከኋላ ላለው ተጫዋች በሚመስል መልኩ ሲያሳልፈው ያገኘው ቃልኪዳን ዘላለም ሳይጠቀምበት ሲቀር በሲዳማዎች በኩል 85ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ በቀለ ከፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 8 ደቂቃዎች ውስጥ ስድስተኛው ደቂቃ ላይ ዐፄዎቹ የአሸናፊነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ጋቶች ፓኖም በድንቅ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በግሩም ቅልጥፍና መልሶበታል። ጨዋታውም 2ለ2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጨዋታው ለተመልካች ሳቢ እንደነበር ጠቁመው በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ያስተናገዱት ግብ ጫና እንደፈጠረባቸው እንዲሁም ቡድናቸው ካለፈው ሳምንት አንፃር ተሻሽሎ መቅረቡን ሲናገሩ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ጨዋታውን ማሸነፍ ይችሉ እንደነበር በመጠቆም በቀላሉ ግብ እንደተቆጠረባቸው እና የግብ ዕድሎችንም ማባከናቸውን ሲገልጹ ከጨዋታው ሂደት አንጻር ማሸነፍ ይገባቸው እንደነበር በመናገር ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ተቀይሮ የወጣው በሠራው ስህተት በተቆጠረበት ጎል ሳይሆን በራስ መተማመኑን አጥቶ ባለመረጋጋቱ እንደሆነ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።