የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ18ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በርካታ ተጫዋቾች ጎልተው በወጡበት የጨዋታ ሳምንት በአንጻራዊነት ብልጫ በወሰዱ ተጫዋቾች ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አሰላለፍ 3-4-1-2

ግብ ጠባቂ

ጽዮን መርዕድ – ሀዋሳ ከተማ

ግብ ጠባቂዎች ጎልተው ባልታዩበት የጨዋታ ሳምንት በአንጻራዊነት ጽዮን መርዕድ የተሻለ ነበር። ኃይቆቹ ብርቱካናማዎቹን 3ለ1 በረቱበት ጨዋታ የግብ ጠባቂው ንቁ ተሳትፎ ለውጤቱ ማማር ድርሻ ነበረው።


ተከላካዮች

ፍሬዘር ካሣ – ባህር ዳር ከተማ

ባህርዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፈበት የጨዋታ ሳምንት የመሐል ተከላካዩ ሚና ከፍ ያለ ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በፈጣን ሽግግር እና በዓየር ላይ ኳሶች ጥቃት በሚሰነዝሩበት ወቅት በተደጋጋሚ የጥቃት ምንጮቹን በማቋረጥ እና በተንጠልጣይ መልኩ ይጣሉ የነበሩትን ኳሶችን በማምከን ጥሩ የጨዋታ ሳምንት አሳልፏል።

ስቴፈን ባዱ አኖርኬ – መቻል

መቻል ከተከታታይ ድል አልባ ጉዞ በኋላ በተጠባቂው የንግድ ባንኩ ጨዋታ ከድል ጋር ሲታረቅ ጋናዊው የመሐል ተከላካይ ጥንካሬ ቀላል የሚባል አልነበረም። በድግግሞሽ ንግድ ባንኮች በረጃጅም ኳሶች የሚያሻግሯቸውን ኳሶች በግንባር ገጭቶ በማምከንም ሆነ በአንድ ለአንድ ግንኙነት የበላይነትን በማሳየቱ በምርጥ ስብስባችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።

በረከት ሳሙኤል – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳዎች ብርቱካናማዎቹን 3ለ1 ሲያሸንፉ የተከላካዩ በረከት ብቃት እጅግ ግሩም ነበር። የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ ብልጫ በመውሰድ እንዲሁም አደገኛ ኳሶችን በማቋረጡ በኩል የተሳካ ቀን ያሳለፈው ተከላካዩ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በግሩም ሸርታቴ ያገደው የሱራፌል ጌታቸው ሙከራ ውጤት ቀያሪ ሊሆን የሚችል ነበር።

አማካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ ሻሸመኔ ከተማን 2ለ0 በመርታት የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መምራት በጀመሩበት ጨዋታ የመስመር ተከላካዩ ዕረፍት የለሽ የሆነ እና ያልተገደበ የማጥቃት እንቅስቃሴ ግሩም ነበር። ከመከላከሉ ባሻገር የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ያደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴም በምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ዮሐንስ መንግሥቱ – መቻል

ከወንድሙ ሀዘን ተመልሶ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የተካተተው ወጣቱ አማካይ ለመቻል የድል ምስጢር ትልቁን ቦታ ይይዛል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማጥቃት መነሻ የነበረውን አማካዩ ባሲሩ ዑመርን በመቆጣጠር እና ከጨዋታ ውጪ በማድረግ መሐል ሜዳው ላይ ብልጫ እንዳይወሰድ በጨዋታ ሳምንቱ ኮከብ ሆኖ ውሏል።

ታፈሰ ሰለሞን – ሀዋሳ ከተማ

በሳምንቱ እጅግ አስደናቂ እንቅስቃሴ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል ታፈሰ ሰለሞን ግንባር ቀደሙ ነው። ፈጣሪው አማካይ ሀዋሳ በዓሊ ሱሌይማን ግቦች ድሬዳዋን 3ለ1 ሲያሸንፍ በርካታ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠሩም በላይ ፈጣኑ አጥቂ ላስቆጠራቸው ሁለት ግቦችም በግሩም ዕይታ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ቦና ዓሊ – አዳማ ከተማ

አዳማዎች ከፍጹም የጨዋታ ብልጫ ጋር ሀምበርቾን 3ለ0 ሲያሸንፉ የአጥቂው ሚና እጅግ የጎላ ነበር። በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻለው ቦና በስሙም ሁለት ግቦችን በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።

ፍሬው ሠለሞን – ባህር ዳር ከተማ

ማራኪ በነበረው የባህር ዳር እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ፍሬው ሠለሞን ደምቆ ውሏል። በቋሚነት ከሚጫወትበት ወደ መስመር እየወጣ ለግብ ምንጭ የሚሆኑ ኳሶችን ለማቀበል ጥረት ሲያደርግ የተስተዋለው አማካዩ ሀብታሙ ታደሠ እና ቸርነት ጉግሳ ላስቆጠሯቸው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ግቦች ያቀበለበት መንገድ የሳምንቱ ምርጥ ስብስባችን አካል እንዲሆን አስችሎታል።

አጥቂዎች

አማኑኤል ኤርቦ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው አጋማሽ ባደረጋቸው ቅያሪዎች ታግዞ ወደ ሊጉ መሪነት የመጣበትን ውጤት ባስመዘገበበት ጨዋታ በአጋማሹ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ኤርቦ ሁለት ግቦችን ከመረብ በማዋሃድ ለቡድኑ ውጤት ካደረገው ከፍ ያለ ድርሻ አኳያ በምርጥ ስብስባችን ውስጥ ተካቷል።

ዓሊ ሱሌይማን – ሀዋሳ ከተማ

ኤርትራዊው የሀዋሳ ከተማ ፈጣን አጥቂ ቡድኑ ድሬዳዋ ላይ የ3ለ1 ድል ሲቀዳጅ እጅግ ስኬታማ ቀን ማሳለፍ ችሏል። ከእንቅስቃሴው ባሻገር ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ መሥራት የቻለው ዓሊ የሊጉን የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ደረጃም በ10 ግቦች መምራት ጀምሯል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

በመቀመጫ ከተማቸው እየተጫወቱ የሚገኙትን እና በግሩም ወቅታዊ ብቃት ላይ ያሉትን ድሬዳዋ ከተማዎች የረቱት ሀዋሳ ከተማዎች አሰልጣኝ የሆኑት ዘርዓይ ሙሉ በተለይም ከ20 ደቂቃዎች በኋላ የመረጡት የጨዋታ መንገድ እጅግ ስኬታማ አድርጓቸዋል። ሆኖም አሰልጣኙ በተጋጣሚያቸው ላይ በወሰዱት ብልጫ ከአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እና ከአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጋር ተፎካክረው የምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ ተመርጠዋል።

ተጠባባቂዎች

መክብብ ደገፉ – ሲዳማ ቡና
መሳይ አገኘሁ – ባህር ዳር ከተማ
ግሩም ሐጎስ – መቻል
በኃይሉ ግርማ – መቻል
የአብሥራ ተስፋዬ – ባህር ዳር ከተማ
ሽመልስ በቀለ – መቻል
ከነዓን ማርክነህ – መቻል
አቤል እንዳለ – ፋሲል ከነማ
ቸርነት ጉግሳ – ባህር ዳር ከተማ
ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ
ብሥራት በቀለ – ወላይታ ድቻ
ማይክል ኪፖሩል – ሲዳማ ቡና