የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ  በተደረጉ ጨዋታዎች ሲቀጥል ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

የረፋድ 3:00 ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቶ ድሬደዋ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ድል አድርጓል። በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎችም ቅዱስ ጊዮርጊስ የጨዋታ በላይነት ወስዷል። እንዲሁም የግብ ሙከራዎችንም አድርገዋል። በዚህም በ6ኛው ደቂቃ ምሕረት ቶንጆ ተከላካዮችን አታልላ በማለፍ ያለቀ ኳስ አሻግራ ተስፋነሽ አዳነ ከመረብ ጋር አገናኝታ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ አድርጋለች።


ድሬዳዋ ከተማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጭነው ኳስ ተቆጠጥረው ተጫውተዋል። የአቻነት ግብ ለማስቆጠርም አስራ ሁለት ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል። በ18ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ በርቀት ላይ አግኝተው ፋሲካ በቀለ ቀጥታ ወደ ግብ በመምታት  ከመረብ ጋር አገናኝታ አቻ ሆነዋል። ድሬዎች የአቻነት ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው በመመለስ ተወስዶባቸው የነበረውን የጨዋታ ብልጫ ማስመለስ ችለዋል።

ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በጫና የተጫወቱት ድሬዎች በ41ኛው ደቂቃ ሰርከአዲስ ጉታ እና ሊድያ ጌትነት በእርስ በርስ ቅብብል በመግባት ሊድያ ጌትነት ከመረብ ጋር አገናኝታ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት በድሬዳዋ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል። ከመልበሻ ክፍል መልስ ድሬዳዋ ከተማ ጥንካሬያቸውን አስቀጥለዋል። ተጨማሪ ግብም እንዲሁ አስቆጥረዋል። በ64ኛው ደቂቃ ቁምነገር ካሳ በመስመር በኩል ኳስ እየገፋች ይዛ ገብታ ለድሬዳዋ ከተማ ተጨማሪ ግብ ከመረብ ጋር አገናኝታ ሶስት ለአንድ እንዲመሩ አስችላለች።

ጊዮርጊሶች ግብ ለማስቆጠር በጫና መጫዎት ችለዋል። ሆኖም ግን ድሬዎች ወደኋላ አፈግፍገው በመጫወታቸው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው 3ለ1 በሆነ ውጤት ተገባዷል።

ከሱ በማስከትል በተደረገው መርሐግብር አዳማ ከተማ ከልደታ ክ/ከተማ ተገናኝተው በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጥሩ ፉክክር የታየበት የአምስት ሰዓቱ ጨዋታ በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አዳማ ከተማ በመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ እንቅሰቃሴ ማድረግ ችሏል። ልደታዎችም በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥር ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ከተጋጣሚያቸው ጋር አድርገዋል። ሆኖም ግን አዳማ ከተማ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ሁለቱም ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት የግብ ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

በ14ኛው ደቂቃ ቤቴል ጢባ ከግብ ክልል ውጭ ሆና አክርራ የመታችው ኳስ ከመረብ ጋር ተገናኝቶ አዳማ ከተማ 1ለ0 መምራት ችሎ ነበረ። ልደታዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም በ26ኛው ደቂቃ በአንድ ለአንድ ቅበብል የተገኘውን ኳስ ማናዐየሽ ተስፋዬ ከመረብ ጋር አገናኝታ የመጀመሪያውን አጋማሽ ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አስችላለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እየተቀዛቀዘ የመጣ ሲሆን አልፈው አልፈው ብቻ የግብ ሙከራዎች በመልሶ መጥቃት ሲደረጉ ለማየት ተችሏል። የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት አዳማዎች ሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ በ47ኛው ደቂቃ ሳባ ኃይለሚካኤል ከመስመር አካባቢ አክርራ በመምታት ግብ አስቆጥራ አዳማ ከተማ 2ለ1 መምራት ችሏል።


ልደታዎች እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግብ ፍለጋ ሙከራ ቢያደርጉም አዳማዎች በመከላከል በመጫወታቸው ግብ ለማስቆጠር ተቸግረዋል። ጨዋታውም በአዳማ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።