ታክቲካዊ ትንታኔ : መብራት ኃይል 2-1 ዳሽን ቢራ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተደርገዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም የተመረጡ ጨዋታዎችን በጥልቀት በመዳሰስ ለእናንተ ለአንባቢያን ማቅረቧን ቀጥላለች፡፡ መብራት ኃይል ዳሽን ቢራን አስተናግዶ 2-1 ያሸነፈበትን ጨዋታ ትንታኔ እንዲህ ባለ መልኩ አቅርበንላችኋል፡፡

ቋሚ አሰላለፍ

መብራት ኃይል( አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ )

ገመቹ በቀለ

አወት ፣ ሲሳይ ፣ በረከት እና አሳልፈው

አዊኪ ማናኮ ፣ ዊልያም ፣ አዲስ (አምበል) እና ወንድሜነህ

ራምኬል ሎክ እና ፒተር

ዳሽን ቢራ(አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ)

ደረጄ አለሙ

አለፍአየሁ ፣ አይናለም (አምበል) ፣ አለማየሁ ፣ አቡሽ

አስራት ፣ ምንያህል እና ሳሙኤል

የተሻ ፣ ተዘራ እና ሀብታሙ

(ምስል – 1)

Electric 2-1 Dashen (1)

መብራት ኃይል

ቀያዮቹ ወደ ሜዳ ይዘውት የገቡትን የተጫዋቾች ባህርይ ስንመለከት ቡድኑ በ4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገባ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ከጨዋታው ጅማሬ በኋላ ወንድሜነህ ወደፊት የተጠጋ 10 ቁጥር ቦታን ሲይዝ ሁለቱ የፊት አጥቂዎች የመስመር አጥቂነትን ሚና (ዋይድ ስትራይከር) ይዘው ሲጫወቱ ተመልከተናል፡፡ ይህም የቡድኑን የሜዳ ላይ አደራደር 4-3-1-2 ወይም 4-3-3 አስመስሎታል፡፡ (ምስል 2)

Electric 2-1 Dashen (2)

የዳሽን ቢራ ወደ አንድ መስመር ያጋደለ አጨዋወት

ዳሽን ቢራ የጨዋታውን 2/3 ክፍለ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ ወደ ቀኝ መስመር አጋድሎ ተጫውቷል፡፡ በዘመናዊው እግርኳስ ቡድኖች በ3 ምክንያቶች ወደ አንድ መስመር ያጋደለ አጨዋወትን ይተገብራሉ፡፡

1ኛ.ወደ አንድ መስመር ኳሱን ለመሰድ እና ተደጋጋሚ ክሮሶችን ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ለማሻገር ያግዛቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ በተክለ ሰውነት ገዘፍ ያሉ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ሴንተር በሚደረጉ ኳሶችአደጋ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ (የቫንሃል ማንቼስተር ዩናይትድ ከግራ መስመር የሚሻሙ ኳሶችን በፌላይኒ አማካኝነት ለመጠቀም ጥረት የሚያደርገው እንደ አንድ ምሳሌ ይጠቀሳል)

2ኛ.በአንድ መስመር ላይ በርካታ ተጫዋቾች በመጠቀም የተጋጣሚን መስመር በመጫን (Over Load በማድረግ) በተቃራኒ መስመር የሚገኘውን ተጫዋች ነፃ ለማድግ ይረዳል፡፡

3ኛ.አንዳንድ ጊዜ ይህ አጨዋወት የአሰልጣኞች የጨዋታ እቅድ ባይሆን እንኳን የተጋጣሚው ቡድን አንደኛው መስመር ደካማ ከሆነ የጨዋታው እንቅስቃሴ ደከም ወዳለው የተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ሊያዘነብል ይችላል፡፡

ከዳሽን ቢራ የእለቱ እንቅስቃሴ በመነሳት አሰልጣን ሳምሶን አየለ አንደኛውን እና ሶስተኛውን ምክንያት ለመጠቀም ያሰቡ ይመስላሉ፡፡ በቀኝ ፉልባከ የተሰለፈው አለፍአየሁ ፣ ከሶስቱ አማካዮች የቀኙን መስመር ይዞ የተሰለፈው ሳሙኤል እና በቀኝ መስመር አጥቂ ቦታ ላይ የተሰለፈው የተሻ አማካኝነት በቀኝ መስመር በኩል በተደጋጋሚ በመብራት ኃይል የግራ መስመር ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን የተሻ እና ሳሙኤል ወደ ሳጥኑ የሚልኳቸው ኳሶችን ተዘራ እና ሀብታሙ ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ (21ኛው እና 33ኛው እና 38ኛው ደቂቃ) ከዚህ ጋር በተያየዘ የመብራት ሶስት አማካዮች ለግራ ፉልባኩ አሳልፈው ሽፋን ለመስጠት ያደረጉት ጥረት አናሳ መሆኑ አሳልፈው እንዲጋለጥ በር ከፍቷል፡፡ (የዳሽን የአቻነት ግብ የተቆጠረው ከዚሁ መስመር በተነሳ ኳስ መሆኑ ልብ ይሏል) በዚህም ምክንያት የመብራት ኃይል የተከላካይ መስመር ወደ ግራ አዘንብሎ ለመከላከል ተገዷል፡፡

የመብራት ተከላካዮች ወደ ግራ ማዘንበል በግራ መስመር (በመብራት ቀኝ) ለተሰለፈው ሀብታሙ እና ከኋላው ለሚገኘው ምንያህል ሰፊ የመጫወቻ ክፍተት ቢፈጥርላቸውም በአግባቡ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ (ምስል 2 ላይ የመብራት ተከላካዮችን አቋቋም እና በኦቫል ቅርፅ የተከበበውን ይመልከቱ)

 

ወንድሜነህ ዘሪሁን

የመብራት ኃይል የማጥቃት ሂደት በሙሉ የሚያልፈው በወንድሜነህ ዘሪሁን በኩል ነበር፡፡ ተጫዋቹ በሃገራችን እንደሚገኙት አጥቂ አማካዮች ሁሉ ትክክለኛ የመጫወቻ ስፍራውን መለየት ቢያስቸግርም የዳሽን ደካማ ቦታዎች ላይ ሁሉ በመገኘት በርካታ 3 ማእኖችን (ትሪያንግልስ) ሲሰራ ተመልክተነዋል፡፡ ራምኬል እና ፒተር ወደ መስመር ያጋደሉ አጥቂዎች በመሆናቸው በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወንድሜነህ በሀሰተኛ 9 ቁጥር አቋቋም ተመልክተነዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዳሽን ደካማ ጎን ወደ ነበረው የቀኝ መስመር በማዘንበል አዲስ እና ዊልያምን ከፒተር ጋር ለማገናኘት (link ለማድረግ) ሞክሯል፡፡ መሃል ለመሃል የሚያደርገው እንቅስቃሴም የዳሸንን የኳስ ፍሰት የሚቆጣጠረው አስራት መገርሳን ሚና በመገደብ ከፊቱ ካሉት አማካዮች እንዲነጠል አድርጓል፡፡

ሌላው ከእረፍት በፊት ሊጠቀስ የሚገባው የመብራት ኃይል ጥንካሬ በርካታ ተጫዋቾች በመስመሮች መካከል መገኘታቸው ነው፡፡ ከአስራት መገርሳ ውጪ ሌሎቹ የዳሽን አማካዮች ወደ ፊት ተጠግተው በመጫወታቸውና ተከላካዮቹ ለግባቸው ቀርበው የሚከላከሉ በመሆናቸው የመብራት አጥቂዎች እና የዳሽን ተከላካዮች ፊት ለፊት የሚፋጠጡበት አጋጣሚ ነበር፡፡ የመጀመርያው የመብራት ኃይል ግብም ለዚህ እንደ አብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ (ምስል 2)

 

ሁለተኛው አጋማሽ

በሁለተኛው አጋማሽ ለ20 ደቀቃዎች ያህል የተጫዋችም ሆነ የታክቲክ ለውጥ አልነበረም፡፡ በ62ኛው ደቂቃ የዮርዳኖስ አባይ በአዊኪ ማናኮ ተቀይሮ መግባት ለአሰልጣኝ አጥናፉ ስኬትን ያመጣ የጎላ ለውጥ ነበር፡፡ ዩጋንዳዊው አማካይ በጨዋታው እምብዛም ተሳትፎ ያልነበረው በመሆኑ ቅያሬው ትክከለኛ ይመስላል፡፡ የዮርዲ መግባት የመብራት ኃይልን የሜዳ ላይ አደራደር ወደ ቀጥተኛ 4-3-3 ለውጦታል፡፡ ከፊት የሚገኙት ሶስቱ አጥቂዎች (ዮርዳኖስ በቀኝ ፣ ራምኬል በመሃል ፣ ፒተር በግራ) ተመሳሳይ አጨዋወትን የሚተገብሩ ሲሆኑ ኳስን በቀጥታ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ይዘው በመግባት አደጋ መፍጠር የሚችሉ ናቸው፡፡ በዳሽን የተከላከይ መስመር እና አማካይ መስመር መከከል የነበረው ርቀት ሰፊ በመሆኑም በቀላሉ አደጋ ለመፍጠር አስችሏቸዋል፡፡

ሌላው በሁለተኛው አጋማሽ የታየው አብይ ለውጥ ወደፊት በተደጋጋሚ ሲያጠቃ የነበረው የአለፍአየሁ እንቅስቃሴ መገደብ ነው፡፡ በተለይም የፒተር የሜዳውን ስፋት ተጠቅሞ መጫወት መቻልና ዊልያም ወደ ግራ አጋድሎ የዳሽንን እንቅስቃሴ ለማቋረጥ መጣሩ ዳሽኖች ከእረፍት በፊት በቦታው የነበራቸውን የበላይነት ለመግታት አስችሏቸዋል፡፡

አሰልጣኝ አጥናፉ በንግድ ባንኩ ጨዋታ ውጤታማ ያደረጋቸውን የማጥቃት ባህርይ ያላቸውን ተጫዋቾች ማብዛት በዚህኛው ጨዋታ ላይም ውጤታማ አድርጓቸዋል፡፡ (ዮርዳኖስ አባይ የማሸነፍያዋን ግብ ለማስቆጠር የፈጀበት 5 ደቂቃዎች ብቻ ነው)

Electric 2-1 Dashen (3)

ያጋሩ