የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታ በሁለቱም ምድቦች ዛሬ ተደርገው ሲጠናቀቁ ኦሮሚያ ፓሊስ ፣ ነገሌ አርሲ ፣ ደሴ ከተማ እና ነቀምት ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል።
ምድብ ሀ
የምድብ የመጨረሻ ቀን ቀዳሚ የነበረው ጨዋታ 8፡00 ሰዓት ሲል ኦሮሚያ ፓሊስን ከሀላባ ከተማ ያገናኘ ነበር። ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክርን መመልከት በቻልንበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ግልፅ የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ በኩል ኦሮሚያ ፓሊሶች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ግልፅ ዕድሎች በብዛት ፈጥረው ተስተውሏል። 9ኛው ደቂቃ ላይ ፈጣኑ አጥቂ ኤፍሬም ሌዳሞ በቀኝ የሜዳው ክፍል ወደ ሳጥን እየነዳ ይዞ የገባውን ኳስ ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከጎሏ በኋላ ወደ አቻነት ለመሸጋገር ሀላባዎች ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በተለይ ስልነት የሚታይባቸው ኦሮሚያ ፓሊሶች ጥራት ያላቸውን ዕድሎች በመፍጠሩ የተዋጣላቸው ሆነዋል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ለተመልካች ሳቢነቱ ሳይደበዝዝ በቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ ኦሮሚያ ፓሊሶች በፈጣን አጥቂዎቻቸው ዕገዛ በርካታ የግብ ሙከራዎችን ማድረጋቸውን ቀጥለው 66ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ድንቅ የነበረው ኤፍሬም ሌዳሞ በተከላካዮች መሐል ነፃ ቦታ ለተገኘው ዳንኤል ዳርጌ አቀብሎት ተጫዋቹ በጥሩ የእግር ሥራ ኳሷን መረቡ ላይ አሳርፏት ጨዋታው በ2ለ0 የኦሮሚያ ፓሊስ ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።
የማሳረጊያ በሆነው እና ሁለቱን የኦሮሚያ ክለቦች ጅማ አባ ቡናን ከነቀምት ከተማ ባገናኘው ጨዋታ ከዕረፍት መልስ የበላይነትን በያዙት ነቀምቶች አሸናፊነት ፍፃሜን ያገኘ ሆኗል። ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ከእንቅስቃሴዎች ውጪ በግብ ሙከራዎች ያልታጀበ ሲሆን ከዕረፍት መልስ ግን ነቀምት ከተማዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር የድል ግቦቻቸውን ማግኘት ችለዋል።
63ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ መንገሻ ከመስመር ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው በፍቃዱ ተፈሪ አለመቆጣሩን ተከትሎ ተመስገን ዱባ አግኝቷት ከመረብ ኳሷን አሳርፎ ነቀምትን መሪ አድርጓል። ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ 90+6 ላይ ሠለሞን ጌታቸው የግል አቅሙን ተጠቅሞ በአግባቡ ያቀበለውን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በቀላሉ በማስቆጠር ጨዋታው በነቀምት ከተማ 2ለ0 ውጤት ተደምድሟል።
ምድብ ለ
በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ረፋዱን በተከናወነው ጨዋታ ነገሌ አርሲ ባቱ ከተማን አሸንፎ ወደ መሪዎቹ ከፍ የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሏል። 3ለ1 በሆነ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ ከዕረፍት በፊት ገብረመስቀል ዱባለ እና ጀቤሳ ሚኤሳ ከዕረፍት መልስ ደግሞ ሠለሞን ገመቹ የነገሌ አርሲን የድል ግቦች ከመረብ ሲያገናኙ ብርሀኑ አዳሙ ባቱዎችን ከሽንፈት ያላዳነች ብቸኛ ግብን አስቆጥሯል።
በማስከተል በተደረገው ጨዋታ በአሰልጣኝ ዳዊት ታደለ የሚመራው ደሴ ከተማ 3ለ1 በሆነ ውጤት ቦዲቲ ከተማን ረቷል። የደሴን ሦስት የድል ግቦች ሙሉጌታ ካሳ አስቆጥሮ ሐትሪክ መስራት ሲችል ሳምሶን ቆልቻ ብቸኛዋን የቦዲቲ ጎል ከመረብ ያሳረፈው ተጫዋች ነው።