የመቻል ስፖርት ክለብ ወቅታዊ ሁኔታ እና የክለቡን ቀጣይ ዕቅድ በተመለከተ በክለቡ የሥራ አመራር ቦርድ መግለጫ ተሰጥቷል።
ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ላይ በመቻል ስፖርት ክለብ ካምፕ ውስጥ በተዘጋጀው መርሐግብር በቅድሚያ የስፖርት ክለቡ ቴክኒክ ቡድን መሪ ሻለቃ ዓለማየሁ ይልማ መቻል ከተመሠረተበት 1936 ዓ.ም ጀምሮ ስለ አመሠራረቱ ፣ ውጣ ውረዶች ፣ እልፍ ስኬቶችን ጨምሮ አጠቃላይ ታሪካዊ ዳራዎችን የተመለከተ ገለጻ በመስጠት አስጀምረውታል።
በመቀጠል መድረኩን የተረከቡት የመቻል ስፖርት ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሰይፈ ጌታሁን በሰጡት መግለጫ አዲሱ ቦርድ ከተመሠረተ ሰባት ወራት እንደሆኑት በመናገር ምሥረታው የተደረገውም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መሪነት እንደሆነ ጠቁመው የቦርድ አባላቶች በተለያዩ ሴክተሮች ሀገር ያስጠሩ ስኬታማ ሰዎች እንደሆኑ በመናገር በይፋም አስተዋውቀዋቸዋል።
በዚህም የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ፀሐይ ሽፈራው ምክትል ፕሬዝዳንት መደረጋቸው እና በቦርድ አባልነት ደግሞ ባለሃብት የሆኑት አቶ ዓሊ አልፎዝ ፣ አቶ በላይነህ ክንዴ ፣ አቶ ካሳሁን ምስጋናው ፣ የራምሴ ጫማ ባለቤት አቶ ዘላለም ሀብቴ ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስትራቴጂክ ፕላን አማካሪ የሆኑት አቶ ታየ ሌንጫ እና የመሳሰሉትን ስመጥር ሰዎች በማካተት በከፍተኛ የአፈጻጸም ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሰይፈ ጌታሁን መቻል በቀጣይ አምስት አመታት ከነበረበት የውጤት ማጣት ቀውስ ተላቅቆ በየዓመቱ ለዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን እንደሚሆን እና በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ምርጥ 20 ክለቦች ውስጥ አንዱ እንደሚያደርጉት ያላቸውን ተስፋ ተናግረው ክለቡ የራሱን አካዳሚ ፣ ስታዲየም ፣ ሙዚየም እና ዘመናዊ የስፖርተኞች ማረፊያም ይገነባል ሲሉ ከዚህ በኋላ በእግርኳስ ፌዴሬሽኑም ሆነ በሌሎች አካላት ሆን ተብለው የሚሠሩ ስህተቶችን አንታገስም በሀሳብ የምንሞግትበት ጊዜ መጥቷል ብለው እንደሚያምኑ እና ከሚዲያ ጋር የሚፈለገውን ያህል ቅርበት እንዳልነበራቸው እና አሁን ያ መስመር ክፍት እንደሚሆን ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
በማስከተል የቦርዱ አባል የሆኑት አቶ አሊ አልፎዚ የቡና ቦርድ አባል ሆነው እንደሠሩ እና አሁንም በድጋፍ እንዳልተለዩ በመናገር መቻል ከሠራዊቱ ባሻገር የሁሉም ሕዝብ ተወካይ መሆኑን በመጠቆም በቀጣይ ወራት የ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ከተሞች ለበርካታ ቀናት በሚቆዩ ደማቅ ዝግጅቶች ለማክበር ማቀዳቸውን ሲገልጹ የስፖርት ሚዲያውም ስፖርቱን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንዳለው እና ያንም በአግባቡ እንዲጠቀምበት አበክረው ገልጸዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ ቴክኒካል ዳይሬክተር የሆኑት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በበኩላቸው “መቻል ለኢትዮጵያ” ወይም “መቻል ለሀገር” በሚል መርሕ በርካታ ቴክኒካል ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው የእግርኳስ ቡድኑን ከሌሎች ጊዜያት ለየት የሚያደርገው በርከት ያሉ የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን በማሟላቱ እንደሆነ ያም በሥራ አመራር ቦርዱ ቁርጠኝነት እንደተደራጀ በመጠቆም እና በቀጣይ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ወደ ቡድናቸው ሊቀላቅሉ እንዳሰቡ ተናግረዋል። ኢንስትራክተሩ አክለውም በተለይ የተለያዩ የግብ ጠባቂ አሰልጣኞችን ወደ ሀገራችን በመምጣት ለመቻል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክለቦች የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ስልጠና የሚሰጡበትን መንገድ ለማመቻቸት እየጣሩ እንደሆነ በመናገር መቻልን ይበልጥ ለማሳደግ ከሀገራዊ ውድድሮች በተጨማሪ ቦታው እና ክለቡ አሁን ይፋ ባይደረግም በኢንተርናሽናል መድረክ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው እና ተቀባይነት ማግኘቱንም በመግለጽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን በማጠናከር ከተለያዩ ሙያተኞች ጋር እየሠራ እንደሆነ አብራርተዋል።
ከመግለጫው በኋላም በጋዜጣዊ መግለጫው የተገኙ የሚዲያ አባላት ጥያቄያቸውን አንስተው ምላሽ ከተሰጠባቸው በኋላ በመቻል ስፖርት ክለብ የሚገኙ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን እና ሙዚየም በኮሎኔል ደረጄ መንግሥቱ መሪነት ጎብኝተው መርሐግብሩ ተጠናቋል።