የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ተስተካካይ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ9ኛ ሳምንት ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአርባምንጭ ከተማ ሀዋሳ ከተማ ከመቻል ተገናኝተው ነጥብ ተጋርተዋል።

5 ሰዓት ላይ በተደረገው መርሐግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአርባምንጭ ተገናኝተው በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ነጥብ ተጋርተዋል። በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ማግባት ሙከራ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ አስመልክተዋል። ንግድ ባንክ የግብ ሙከራ በማድረግ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ግን የሚገኙትን አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። አርባምንጭ ከተማም በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርግም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ጠንከር ብለው የገቡት አርባምንጭ ከተማዎች ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ሆነዋል። በ55ኛው ደቂቃ ፎዚያ መሐመድ ርቀት ላይ ሆና ግብ አስቆጥራ አርባምንጭ ከተማን መሪ አድርጋለች። ንግድ ባንኮች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ጫና ፈጥረው ኳስ መስረተው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ወደ መገባደጃ ሲደርስ በ86ኛው ደቂቃ አሪያት ኡዶንግ በመስመር በኩል ይዛ በመግባት ያሻገረቺውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ከመረብ ጋር አገናኝታው ጨዋታው 1ለ1 እንዲያልቅ አድርጋለች።

ሌላኛው ተጠባቂው ሀዋሳ ከተማን ከመቻል ያገናኘው ጨዋታ ስድስት ግቦች ቢቆጠርበትም ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል።

ጥሩ ፉክክር የታየበት የ8:00 ሰዓቱ ሌላኛው መርሐግብር ከዕረፍት በፊትና ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ስድስት ግቦች ነጥብ በመጋራት ሊጠናቀቅ ተገዷል። በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ብቻ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች ሲደረጉ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ሀዋሳ ከተማዎች ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ነበሩ። በ12ኛው ደቂቃ በእርስ በርስ ቅብብል የተገኘውን ኳስ እፀገነት ግርማ ከመረብ ጋር አገናኝታው ሀዋሳ ከተማን ቀዳሚ አድርጋለች።

ምንም እንኳን የግብ ማግባት ብልጫ ቢወሰድባቸውም ጠንከር ብለው ወደ ጨዋታ የገቡት መቻሎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ስምንት ደቂቃ ነበር የጠበቁት። በ20ኛው ደቂቃ ንግሥት በቀለ በመስመር በኩል የሀዋሳን ተከላካዮች እያታለለች ወደ ግብ ክልል ገብታ ያለቀ ኳስ ቀንሳላት ቤተልሔም ታምሩ ወደ ግብነት ቀይራው አቻ እንዲሆኑ ስታደርግ 1ለ1 በሆነ ውጤትም ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ መቻሎች ተወስዶባቻው የነበረውን ብልጫ አስመልሰዋል። ሀዋሳም በአንፃሩ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ኳስን መስርተው ለመጫወት ሲጥሩ ተስተውለዋል። መቻሎችም ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ቡድን ሲገቡ የተስተዋሉ ሲሆን በ53ኛው ደቂቃ ስንታየሁ ኢርኮ ከመስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሯ በመግጨት ከመረብ ጋር በማገናኘቷ መቻሎች መሪነቱን እንዲረከቡ እና ጨዋታው ክብደቱ እና ፉክክሩ እየጨመረ እንዲሄድ ሆኗል። ሁለቱም ቡድኖችም የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብለው ተገኝተዋል።


በ76ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ትዕግሥት ቴቃ ርቀት ላይ ሆና በመምታት ግሩም ግብ ለሀዋሳ አስቆጥራ ጨዋታው አቻ እንዲሆን አድርጋለች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃዎች ሲቀሩት በ80ኛው ደቂቃ በንክኪ የተገኘውን ኳስ እሙሽ ዳንኤል ከመረብ ጋር አገናኝታው ሀዋሳ ከተማ 3ለ2 በመሆን ዳግም መምራት እንዲችል አስችላለች። በዚህ ውጤት መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ ሊታይ ሲል ጥሩ እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረቺው ገነት ኃይሉ ርቀት ላይ አክርራ በመምታት ኳስና መረብ አገናኝታ ጨዋታው 3ለ3 በሆነ ወጤት ተጠናቋል።