ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነቱን አጠናክሯል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ”ሀ” 17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነቱን ሲያጠናክር ቤንች ማጂ ቡናም ድል ቀንቶታል።

ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት በረፋዱ ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡና ከአዲስ አበባ ከተማ ተገናኝተው በቤንች ማጂ ቡና የበላይነት ተጠናቋል።

ቤንች ማጂ ቡና በመጀመሪያ አጋማሽ ፍፁም የጨዋታ በላይነት ወስዷል። አዲስ አበባ ከተማ በአንፃሩ ደካማ እንቅሰቃሴ ያደረገበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፏል። በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩት ቤንች ማጂ ቡናዎች በሰባተኛው ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት መምቻ መስመር ጫፍ ላይ ዳግም ሰለሞን ላይ በተሰራው ጥፋት ቅጣት ምት ለቤንች ማጂ ቡና ተሰጥቷቸው ራሱ ዳግም ሰለሞን በመምታት ግሩም የቅጣት ምት ግብ ከመረብ አገናኝቶ መሪ እንዲሆኑ አስችሏል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት አዲስ አበባ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ኳስን ይዘው በሚገቡበት ቅፅበት በ36ኛው ደቂቃ ቢኒያም ፀጋዬ ላይ በተሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አዲስ አበባ ከተማዎች አግኝተው ኤርሚያስ ኃይሉ መረብ ላይ አሳርፎ አንድ ዕኩል አድርጓቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲልም በ41ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ዳግም ሰለሞን ያሻማውን ኳስ በዕውቀቱ ማሞ በግንባር ገጭቶ ሌላኛውን ግብ ለቤንች ማጂ ቡና አክሎ 2ለ1 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ቤንች ማጂ ቡናዎች ጠንከር ብለው በመመለስ መሪነታቸውን ማስፋት የቻሉበትን ግብ አክለዋል። ናትናኤል በርሄ ያሻማውን ኳስ ዘላለም በየነ 70ኛው ደቂቃ ላይ ለቤንች ማጂ ቡና ሶስተኛውን ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ማስፋት ችሏል። አዲስ አበባ ከተማ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርጓል። የግብ ልዩነት ማጥበብ የቻሉበትን ግብ ተቀይሮ የገባው ረመዳን ናስር በንክኪ የተገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ 3ለ2 በመሆን በመነቃቃት እንዲጫወቱ ቢያደርግም መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አልቆ ተጨማሪ በታየው በ90+2ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ በቀለ ርቀት ላይ ሆኖ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 4ለ2 በሆነ ውጤት ተገባዷል።

የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ወልዲያ ከተማን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቶ ኤሌክትሪኮች መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

ጥሩ ፉክክር ከበርካታ ሀዋሳ ከተማ  ነዋሪ እግር ኳስ ታዳሚዎች ጋር የታጀበው ይሄኛው ጨዋታ ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ እና እልህ አስጨራሽ ፉክክር ያስመለከተ ጨዋታ ነበር። በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ጥሩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ግብ ለማስቆጠር ስድስት ደቂቃ ብቻ ነበር የጠበቁት። በ6ኛው ደቂቃ ናትናኤል ሰለሞን ከመሃል ሜዳ እየገፋ ይዞ ገብቶ ከተከላካዮች ጀርባ ከፍ አድርጎ ያቀበለውን ኳስ የፊት መስመር ተጫዋቹ አቤል ሀብታሙ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮት ኤሌክትሪክን መሪ አድርጓል። ግብ ተቆጥሮባቸውም ተስፋ ያልቆረጡት ወልዲያዎች ጫና ፈጥረው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

ወልዲያዎች በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛው ጨዋታ ክፍለጊዜ እስኪጠናቀቅ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ሆኖም ግን በ45+2ኛው ደቂቃ በአንድ ለአንድ ቅበብል የተገኘውን ኳስ አለኝታ ማርቆስ ከመረብ ጋር አገናኝቷል። በዚህም የመጀመሪያውን አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በጥሩ እንቅስቃሴ ከግቦች ጋር ታጅበው በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ግለቱ እየጨመረ ከመጀመሪያው አጋማሽ የበለጠ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመልካች አስመልክቷል። ኢትዮ ኤሌክትሪክም መሪነቱን ለማጠናከር ጠንከር ብሎ በመግባት የግብ ሙከራዎችን ሲያደርግም ተስተውሏል። በ49ኛው ደቂቃ ግዙፉ የፊት መስመር ተጫዋች መሳይ ሰለሞን ያሬድ የማነ ከመስመር ያሻማትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድጋሚ እንዲመራ አድርጓል። ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጫና የፈጠሩት ኤሌክትሪኮች ሌላኛውን ግብ ለማስቆጠር 6 ደቂቃ ብቻ ነበር የቆዩት።


በ55ኛው ደቂቃ አቤል ሀብታሙ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲመልስበት ኳሷን ሲጠብቅ የነበረው መሳይ ሰለሞን አስቆጥሯት መሪነታቸው አስፍቷል። ወልዲያ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም ኤሌክትሪኮች ወደኋላ አፈግፍገው በመጫወታቸው ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በ84ኛው ደቂቃ በንክኪ የተገኘውን ኳስ ቢኒያም ላንቃሞ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ወልዲያዎች ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ማድረግ ቢችልም ሌላ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 3ለ2 በሆነ ውጤት በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል።