በአስራ ዘጠነኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎችን አስመልክቶ ተከታዮቹን መረጃዎች ልናጋራችሁ ወደናል።
አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ሊጉ አናት ለመመለስ አዳማዎች ደግሞ ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ለመጠጋት አልመው የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።
በመጨረሻው ሳምንት ሀምበርቾችን አሸንፈው ነጥባቸውን ሀያ ሰባት ማድረስ የቻሉት አዳማ ከተማዎች በ7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የውድድር አጋማሽ ዝውውር ያልፈጸሙት አዳማዎች ግቦችን ለማስቆጠር የማይቸገሩ ስል አጥቂዎች ይዘዋል ፤ ሆኖም በአምስት ጨዋታዎች ብቻ መረቡን ሳያስደፍር የወጣውና በውድድር ዓመቱ ሀያ አንድ ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል ለውጦችን ይሻል። ቡድኑ ሀምበርቾን ሦስት ለባዶ ካሸነፈበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ በፊት ባካሄዳቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ድል ፣ ሦስት አቻና አንድ ሽንፈት ቢያስተናግድም አስራ አንድ ግቦች ማስተናገዱና በተጠቀሱት ጨዋታዎች በተከታታይ ግቡን ሳያስደፍር አለመውጣቱ ሲታይ የተከላካይ ክፍሉ ለውጦች እንደሚያስፈልጉት የሚጠቁም ነው።
ቡድኑ የፊት መስመሩ ጥንካሬን ከማስቀጠል ባለፈ በአንፃራዊነት ክፍተት የሚስተዋልበት የኋላ ክፍል ካሻሻለ የነጥብ መጠኑን ይበልጥ እንዲያሻሽል በር ከፋች ሊሆንለት ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ የነገው ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ያለ የፊት መስመር ያለው ቡድን መሆኑም አዳማዎች የኋላ ክፍላቸውን ድክመት እንዲፈትሹ የሚያስገድድ ሌላ ምክንያት ነው።
ተከታታይ አራት ጨዋታዎች አሸንፈው ወደ ሊጉ አናት የተመለሱት ፈረሰኞቹ በመሪነት ለመቆየት የሚያስችላቸውን ነጥብ ከነገው ጨዋታ ይጠብቃሉ። ፈረሰኞቹ ከተከታታይ ድል በዘለለ በጉልህ የሚታይ ለውጥ አምጥተዋል። ቡድኑ ከመጨረሻው ሽንፈት በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስት ድልና አንድ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል ፤ ይህ ማለት ቡድኑ ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥብ ሁለት ብቻ ጥሎ አስራ ስድስቱን አሳክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በተጠቀሱት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ አስተናግዶ አስራ ሁለት ግቦች ማስቆጠሩ ቡድኑ በውጤት ጎዳና እንዳለ አመላካች ናቸው።
ሆኖም በሂደት ወጥነት ያለው ጥሩ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከወራት በፊት ሊጉ ከሀገራት ውድድር ሲመለስ ያጋጠማቸው መቀዛቀዝና የውጤት መጥፋት ችግር አሁንም እንዳይፈጠር የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ በወርሀ ታህሳስ ከነበረው የሀገራት ጨዋታ መልስ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት ፣ ሁለት አቻና አንድ ድል ማስመዝገቡም ይታወሳል። ፈረሰኞቹ በቀጣይ የነገውን ጨዋታ ጨምሮ ከመቻል ፣ ባህርዳር ከተማ ፣ ወላይታ ድቻና ሀዋሳ ከተማ የሚያደርጓቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች የዋንጫ ጉዟቸውን ይወስናሉ ተብሎም ይታሰባል።
በአዳማ ከተማ በኩል ቅጣት ላይ ከሚገኘው አድናን ረሻድ ውጭ የተቀሩት ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆኑ ለማወቅ ችለናል። በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ ከጉዳት ተመልሶ ልምምድ የጀመረው ተገኑ ተሾመ በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ፤ በልምምድ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረው ቢንያም በላይም በነገው ጨዋታ ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሀድያ ሆሳዕና ከ ሀምበርቾ
ከአቻ ውጤት ለመላቀቅ ወደ ሜዳ የሚገቡት ሀድያዎችና በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ለማለምለም ከወዲሁ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሀምበርቾዎች ምሽት ላይ ይገናኛሉ።
በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ተካፍለው በመውጣት በውድድር ዓመቱ ያስመዘገቡት የአቻ ውጤት አስራ ሁለት ያደረሱት ሀድያ ሆሳዕናዎች ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ሀምበርቾን ይገጥማሉ።
በሀያ አራት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያዎች በውድድር ዓመቱ ሁለት ሽንፈቶች ብቻ ቢያስተናግዱም አብዛኛው ጊዜያቸውን በመሃል ሰፋሪነት ነው ያሳለፉት ፤ ለዚ እንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ቡድኑ ከተከታታይ አቻዎች መላቀቅ ባለመቻሉ ነው። ቡድኑ መከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መከተሉ በርከት ያሉ ግቦች እንዳያስተናግድ ቢያግዘውም በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ለአጨዋወቱ ታማኝ መሆናቸውና ውስን ለውጦች አለማድረጋቸው ግን ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል። ቡድኑ የጥራት ደረጃቸው በአንፃራዊነት ወረድ ካሉ ቡድኖች በሚገጥምበት ወቅትም ጭምር በተሻለ መንገድ ማጥቃት ሲገባው ለመከላከሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መጫወቱም በርከት ያሉ ግቦች እንዳያስቆጥር አግዶታል። ሀድያ ሆሳዕናዎች ነጥባቸውን ከፍ አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ከፍ የማድረግ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ሀምበርቾ በ18 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ አንድ ብቻ ድል ያስመዘገበ ብቸኛው ክለብ ነው። እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ሀምበርቾዎች አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን ቢቀጥሩም ከአሰልጣኙ ጋር የነበራቸው እህል ውሀ መዝለቅ አልቻለም። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር ጠንክሮ ለመቅረብ አምስት ተጫዋቾችን አስፈርሞ ከባዱን ፈተና ለመጋፈጥ ቢጥርም ወደ ድል መንገድ መምጣት አልተቻለውም። ቡድኑ በሁለቱም የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ያለው ድክመትም አሁን ላለበት ደረጃ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል። ዝቅተኛው የግብ መጠን (7) በማስመዝገብና ከፍተኛው የግብ መጠን(28) በማስተናገድ በሁለቱም መለኪያዎች ደካማ የሆነው ቡድኑ ይህንን ችግሩን በቶሎ ፈቶ ነገ ከናፈቀው ድል ጋር የማይገናኝ ከሆነ ለከርሞ በሊጉ የመቆየቱ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ይሆናል።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል ግርማ በቀለ እና መለሠ ሚሻሞ በጉዳት ምክንያት በጨዋታው አይሳተፉም። የዳግም በቀለ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።