ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ገዛኸኝ ደሳለኝ በራሱ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሻሸመኔ ከተማን 1ለ0 ረተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሲዳማ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ ሲገናኙ ሲዳማዎች በ18ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር 2ለ2 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ጉዳት ላይ የሚገኙት ጊት ጋትኩት እና ይገዙ ቦጋለ ወጥተው አንተነህ ተስፋዬ እና ይስሃቅ ካኖ ተተክተው ገብተዋል። በተመሳሳይ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ0 የተሸነፉት ሻሸመኔዎች በአንጻሩ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ማይክል ኔልሰን ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ፣ ኢዮብ ገብረማርያም እና ስንታየሁ መንግሥቱ ወጥተው ሄኖክ ድልቢ ፣ ጌታለም ማሙዬ ፣ አብዱልቃድር ናስር እና አብዱልከሪም ቃሲም በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብተዋል።

ምሽት 1 ሰዓል ሲል በቅርቡ ሕይወቱ ላለፈው የባህር ዳር ከተማ አማካይ አለልኝ አዘነ የሕሊና ጸሎት ተደርጎ በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በጥሩ ግለት ጅማሮ ያደረጉት ሲዳማዎች በጨዋታው መሪ መሆን የቻሉት ገና በ4ኛው ደቂቃ ነበር። ማይክል ኪፖሩል ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የሻሸመኔው ተከላካይ ገዛኸኝ ደሳለኝ ለማቋረጥ ሲሞክር ኳሱን የራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የተቸገሩት ሻሸመኔ ከተማዎች የአጋማሹን የተሻለ የመጀመሪያ የግብ ዕድላቸውን 17ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረው አብዱልከሪም ቃሲም ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ይዞበታል። ያንኑ ኳስ በመልሶ ማጥቃት የወሰዱት ሲዳማዎችም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ማይክል ኪፖሩል በግሩም ክህሎት በሳጥኑ የግራ ክፍል ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል።

በሁለቱም የማጥቂያ መስመሮች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች 23ኛው ደቂቃ ላይም ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ይስሃቅ ካኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ አግዶበታል። በአስር ደቂቃዎች ልዩነትም በዛብህ መለዮ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

40ኛው ደቂቃ ላይ የመሃል ተከላካያቸውን ምንተስኖት ከበደን በጉዳት ምክንያት በአሸብር ውሮ ለመቀየር የተገደዱት ሻሸመኔዎች በደቂቃ ልዩነት ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። ሀብታሙ ንጉሤ ሳጥን ውስጥ ይስሃቅ ካኖ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ደስታ ዮሐንስ ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲን አታልሎ በግራ በኩል እንዲወድቅ ቢያርግም ኳሱን የቀኙ ቋሚ መልሶበታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ደግሞ የሻሸመኔው አብዱልከሪም ቃሲም ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ አስወጥቶበታል።


ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ሻሸመኔዎች በኳስ ቁጥጥሩ በመጠኑ ተሻሽለው ቢቀርቡም በሲዳማዎች በኩል 51ኛው እና 90+1ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን እና አበባየሁ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ሞክረውት ግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዛቸው 72ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ አሻግሮት አቅጣጫ ቀይሮ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰው እና ተቀይሮ የገባው ይገዙ ቦጋለ ሳያገኘው ከቀረው ኳስ ውጪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ የሚችሉትን እንዳደረጉ እና ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ሆኖም በጋራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ክፍተት እንዳዩ ሲናገሩ ኳስ ይዘው መጫወታቸውን እና ግብ ማስቆጠር ብቻ እንደጎደላቸው በመጠቆም የፍጹም ቅጣት ምቱ መሳት ዕድለኛ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል። ድል የቀናቸው የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠራቸውን ተናግረው ውጤቱን ፍለጋ በመጓጓት የመረጋጋት ችግር እንደነበረባቸው ሲናገሩ በራስ ላይ የተቆጠረው ግብ ዕድለኛ እንደማያስብላቸው እና በእንቅስቃሴያቸው ምክንያት የተቆጠረ መሆኑን በመጠቆም ድሉንም ጨዋታውን ስታዲየም ተገኝተው ለተከታተሉት ለአዲሱ የቦርድ ኃላፊ አበርክተዋል።