የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ19ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ19ኛው የጨዋታ ሳምንት ጎልተው በወጡ ተጫዋቾች ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

መክብብ ደገፉ – ሲዳማ ቡና

ተቀራራቢ አቋም ያሳዩ ግብ ጠባቂዎች በታዩበት የአስራ ዘጠነኛው ሳምንት ጨዋታ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ከወጡት መካከል በአንፃራዊነት ጥሩ ግልጋሎት የሰጠውን የሲዳማ ቡናው መክብብ ደገፉን ተመራጭ አድርገናል። መክብብ ምንም እንኳን በርከት ያሉ ጥቃቶች ባይሰነዘሩበትም የጨዋታው መልክ ሊቀይሩ የሚችሉ ሙከራዎችን ከማዳኑ ባሻገር ከኋላ በመሆን ቡድኑን በማደራጀት ካሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ አኳያ ከታፔ አልዛየር ጋር በመፎካከር ተመራጭ ሆኗል።

ተከላካዮች

አብዱልከሪም መሐመድ – ኢትዮጵያ መድን

ወደ ቀኝ ባዘነበለው የኢትዮጵያ  መድን የማጥቃት ጥረት ውስጥ ታታሪው አብዱልከሪም እንደሁልጊዜው ወደ ፊት በመሄድ ተሳትፎ ሲያደርግ ታይቷል። የሀዋሳ ከነማን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያቋርጥ የቆየው አብዱልከሪም ቡድኑ ከጨዋታው የሚመኘውን ሦስት ነጥብ ማሳካት ባይችልም ቢያንስ አንድ ነጥብ በማግኘቱ ረገድ የነበረው ሚና የጎላ በመሆኑ ከበረከት ወልደዮሐንስ ጋር በመወዳደር ምርጫ ውስጥ ሊካተት ችሏል።

ቃልአብ ውብሸት – ሀዲያ ሆሳዕና

በጉዳት እና በአሰልጣኞች ምርጫ በዘንድሮ ዓመት ለቡድኑ ብዙ ግልጋሎት ሳይሰጥ የቆየው ወጣቱ ተከላካይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በመግባት የቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ ላይ ተጨማሪ አቅም ይዞ መምጣቱን እያሳየ ይገኛል። በተለይ የጨዋታውን መልክ ሊቀይር የሚችለውን ወርቃማ አጋጣሚ ሀምበርቾዎች በአልዓዛር አድማሱ አማካኝነት አግኝተው ግብ ጠባቂውን ታፔ አልዛየርን አልፎ ወደ ጎልነት ሊቀየር የነበረውን ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና ያገደበት መንገድ ድንቅ ነበር።

አስቻለው ታመነ – መቻል

በዚህ ሳምንት ከታዩ የመሐል ተከላካዮች መካከል እንደ አስቻለው ታመነ ጥሩ ብቃት ያሳየ ተከላካይ አልተመለከትንም ቢባል ማጋነን አይሆንም። አስቻለው በከፍተኛ ትኩረት ጨዋታውን በማድረግ በአንድ ለአንድ ግንኙነት በማሸነፍ ፣ ተሻጋሪ ኳሶችን በማቋረጥ ፣ ጊዜያቸውን የጠበቁ ሸርታቴዎችን በማድረግ ግሩም እንቅስቃሴ አድርጓል። እንደ አማካይ ተጫዋች ስኬታማ የሆኑ ኳሶችን በረዥሙ ወደ ፊት ያቀርብበት የነበረው መንገድ ልዩ ከመሆኑ ባሻገር መቻሎች ላስቆጠሯት ብቸኛ ጎል የመጀመርያው መነሻ ኳስ የአስቻለው ታመነ ድንቅ አቅርቦት ነበር።

አህመድ ረሺድ – አዳማ ከተማ

ምንም እንኳን አህመድ ለቡድኑ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው በመሐል ተከላካይነት ቢሆንም በጨዋታው ካሳየው ድንቅ እንቅስቃሴው አንፃር ልናካትተው ችለናል። ያለፉትን ሁለት ዓመታት ቀድሞ ከነበረው ብቃቱ በተለያዩ ምክንያቶች ወጣ ገባ ሲል የነበረው አህመድ አሁን ወደ ትክክለኛው አቋሙ እየተመለሰ መሆኑን በተከታታይ ጨዋታዎቹ እያሳየን ይገኛል። አዳማዎች 2ለ1 ባሸነፉበት ጨዋታም ፈረሰኞቹ ወደ ጨዋታው እንዳይመለሱ በማድረግም ሆነ ቡድኑ ወሳኝ ድል እንዲቀዳጅ በማስቻሉ በምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ሊካተት ችሏል።

አማካዮች

ሙሴ ኪሮስ – አዳማ ከተማ

በቅርብ ጨዋታዎች የመጫወት ዕድል እያገኘ በ8 ጨዋታዎች ላይ በአማካይ 42 ደቂቃዎችን መጫወት የቻለው አማካዩ አዳማ ከሰባት ዓመታት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ1 ሲያሸንፍ ካደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴ ባሻገር የቡድኑን የመጀመሪያ ግብም በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።

ሽመልስ በቀለ – መቻል

መቻሎች ወላይታ ድቻን እንደ መጀመሪያው ዙር ሁሉ 1ለ0 አሸንፈው የደረጃ ሰንጠረዡን መሪነት በተረከቡበት ጨዋታ ሜዳው በዝናብ ምክንያት ለጨዋታ ምቹ ያልነበረ ቢሆንም ሽመልስ በቀለ ግን ጎልቶ መታየት ችሏል። የማጥቃት እንቅስቃሴውን ሲያሳልጥ የነበረው አማካዩ ምንይሉ ወንድሙ ላስቆጠራት ግብም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ወገኔ ገዛኸኝ – ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጵያ መድን ምንም እንኳን በዘንድሮው የውድድር ዘመን እንደ ቡድን ደካማ ጊዜን እያሳለፉ ቢገኙም ወገኔ ግን በግሉ እጅግ አስደናቂ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ለቡድኑ የአቻነቷን ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በጨዋታው የተሻሉ ለነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች አጠቃላይ የቡድኑን የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት ጨዋታ ያሳለጠበት መንገድ የቡድናችን አካል እንድናደርገው አስገድዶናል።

አጥቂዎች

ዳዋ ሆቴሳ – ሀዲያ ሆሳዕና

ነብሮቹ ሀምበርቾን 2ለ0 ሲያሸንፉ የዳዋ እንቅስቃሴ የሚያስደንቅ ነበር። ወደ ኋላ እየተሳበ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማደራጀቱ በኩል የተካነው አጥቂው ተመስገን ብርሃኑ ላስቆጠራት ግብ አመቻችቶ ማቀበል ሲችል የቡድኑን ሁለተኛ ግብም በተረጋጋ አጨራረስ ማስቆጠር በመቻሉ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ሆኗል።

ቢኒያም ዐይተን – አዳማ ከተማ

በዘንድሮው ውድድር ለአዳማ ከተማ በሙሉ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ካደረጉ አራት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ቢኒያም ዐይተን ቡድኑ ጊዮርጊስን ከ7 ዓመታት በኋላ 2ለ1 በሆነ ውጤት ሲረታ ካደረገው ዕረፍት የለሽ የሆነ እንቅስቃሴ ባሻገር የቡድኑን ሁለተኛ ግብም እጅግ አስደናቂ በሆነ እና ራሱ ባስጀመረው የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ግብ ጠባቂ ጭምር በማለፍ በግሩም ሁኔታ በውድድር ዓመቱ አምስተኛ የሆነውን ግቡን ማስቆጠር ችሏል።

ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ

በሰባት ግቦች የአዳማ ከተማ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ዮሴፍ ታረቀኝ በየጨዋታዎቹ ላይ ከሚያስቆጥራቸው ግቦች ባሻገር ለቡድን አጋሮቹ የሚያመቻቻቸው ኳሶች ትኩረት ሳቢ እየሆኑ መጥተዋል። ሆኖም ተጫዋቹ አዳማዎች ፈረሰኞቹን 2ለ1 በረቱበት ጨዋታ ለመጀመሪያው የሙሴ ኪሮስ እና ለሁለተኛው የቢኒያም ዐይተን ግብ በግሩም ክህሎት አመቻትቶ ማቀበል መቻሉ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርጎታል።

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ ከ7 ዓመታት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሸንፍ አሰልጣኝ ይታገሱ በተጋጣሚያቸው ላይ የወሰዱት ብልጫ አድናቆት የሚያስቸር ነበር። ፈረሰኞቹ ድል አድርገው ወደ ደረጃው አናት ለመመለስ አልመው በገቡበት ጨዋታ የአዳማዎች የሙሉ ደቂቃ ዕረፍት የለሽ የሆነ እንቅስቃሴ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር። በዚህም ምክንያት አሰልጣኙ የዚህን ሳምንት ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ መርጠናቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ታፔ አልዛየር – ሀዲያ ሆሳዕና
አብዱለጢፍ መሐመድ – ድሬዳዋ ከተማ
በረከት ወልደዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና
ጋቶች ፓኖም – ፋሲል ከነማ
ከነዓን ማርክነህ – መቻል
ምንይሉ ወንድሙ – መቻል
መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና
ዓሊ ሱሌይማን – ሀዋሳ ከተማ