የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የ19ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ተደርገው አርባምንጭ ከተማ እና ባቱ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
አምስት ሰዓት ላይ የተካሄደው የባቱ ከተማ እና ካፋ ቡና ጨዋታ በባቱ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው የተሻለ የበላይነት የነበራቸው ባቱ ከተማዎች መሪ የሚሆኑበትን ጎል ማግኘት የቻሉት ገና በጨዋታው ጅማሮ ነበር። ሦስተኛው ደቂቃ ላይ በባቱ የግብ ክልል የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ኢያሱ ተካ በቀጥታ ወደ ካፋ የግብ ክልል መትቶ የካፋው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት አሰግድ ዝንጉነት ታክሎበት በቀጥታ ወደ ጎልነት ተቀይሯል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጨዋታው እንደ አየር ሁኔታው ሁሉ ቀዝቃዛ መልክ የነበረው ቢሆንም ባቱ ከተማዎች የተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በካፋ በኩል ደግሞ በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ከያዘበት ሙከራ ውጪ ሆኖም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ሳንመለከት የመጀመርያው አጋማሽ በባቱ መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስም ጨዋታው የመጀመርያው አጋማሽ መልክ የነበረው ሲሆን በአንፃራዊነት ብልጫ የነበራቸው ባቱዎች በተሻለ ወደ ግብ በመድረስ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይ በ50ኛው ደቂቃ እስራኤል ሻጎሌ በግሩም ሁኔታ ከመስመር ወደ ውስጥ ገብቶ ያመቻቸለትን ኳስ ዮሐንስ ደረጄ ያመከነው አጋጣሚ የሚጠቀስ ነው። በተጨማሪም ዮሐንስ በ76ኛ ደቂቃ ከሳጥኑ ጠርዝ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስም መሪነታቸውን ሊያሰፉበት የሚችሉት አጋጣሚ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በ78ኛው ደቂቃ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የዋለው እስራኤል ከቀኝ መስመር ያመቻቸለተን ኳስ አማኑኤል ተፈራ ቺፕ አድርጎ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር የባቱን መሪነት አስፍቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በባቱ 2-0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
በመቀጠል በተደረገው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ደሴ ከተማን ከመመራት ተነስቶ 5-1 በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የሚያደርገውን ግስጋሴ አጠናክሮ ቀጥሏል።
በጎሎች በታጀበው ጨዋታ ቀዳሚ መሆን የቻሉቴ ደሴዎች ናቸው። በስድስተኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት ይዘው የሄዱትን ኳስ የኋላሸት ፍቃዱ አጨራረሱን በማሳመር ደሴን መሪ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ አርባምንጮች ምላሽ ለመስጠት ጥረት ያደረጉ ሲሆን ብዙም ሳይቆዩ በ13ኛው ደቂቃ አሸናፊ ተገኝ ከመስመር የተሻ ረለትን ኳስ ከመረብ አገናኝቶ አዞዎቹ ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።
ከጎሎቹ በኋላ ጥሩ ኤንቅስቃሴ ያስመለከተን ጨዋታ በቀሪው የአጋማሽ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት በአቻ ውጤት ወደ እረፍት አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ የአርባምንጭ ከተማ የበላይነት የታየበት ነበር። አጋማሹ ገና ሁለት ደቂቃ እንዳስቆጠረም የመጀመርያ ጎል አስቆጣሪው አሸናፊ ተገኝ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ማስቆጠር አርባምንጭን ወደ መሪነት አሸጋግሯል።
ከጎሉ በኋላ አዞዎቹ ይበልጥ ተነቃቅተው ተደጋጋሚ ጫናዎችን መፍጠር ሲችሉ ደሴዎች በአንፃሩ መረጋጋት ተስኗቸው ተስተውተለዋል። በ65ኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ መኮንን ከጥልቅ የሻገረትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ተገናኝቶ ወደ ግብነት ሲቀይር ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አማካዩ እንዳልካቸው መስፍን ከቅጣት ምት ግሩም ጎል አስቆጥሮ መሪነቱን አስፍቷል።
የአርባምንጭ የበላይነት ቀጥሎ ከተደጋጋሚ የማጥቃት ጥረቶች በኋላ በ79ኛው ደቂቃ ፍቃዱ መኮንን በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ የሄደውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 5-1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ድሉን ተከትሎ በውድድር ዘመኑ ሽንፈት ያልገጠመው አርባምንጭ ከተማ ነገ ጨዋታውን ከሚያደርገው ነጌሌ አርሲ ያለውን ልዩነት ወደ 11 ከፍ በማድረግ መሪነቱን አጠናክሯል።