በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የ18ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን መርሐ ግብር ነገሌ አርሲ እና ወሎ ኮምቦልቻ ወሳኝ ድል ሲያስመዘግቡ አዲስ ከተማ እና ቦዲቲ ነጥብ ተጋርተዋል።
የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በቦዲቲ ከተማ እና አዲስ ከተማ ክ/ከተማ መካከል ተካሂዶ ያለ ጎል ተጠናቋል።
በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩት ቦዲቲዎች በሙከራዎች ባይታጀብም ወደፊት ያመዘነ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። በ24ኛው ደቂቃ ጥበቡ ከበደ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበትም በቦዲቲ በኩል ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በሂደት አዲስ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ቅኝት በመግባት የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን በ35ኛው ደቂቃ ቅዱስ ተስፋዬ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን ቅጣት ምት ራሱ መትቶ በግቡ አናት የወጣበት ሙከራ የሚጠቀስ ነው። በመጨረሻዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎችም በተደጋጋሚ ወደ ግብ መቅረብ ቢችሉም የተሳካ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ወደ እረፍት አምርተዋል።
ከእረፍት መልስም እንደ መጀመርያው ሁሉ ብዙም ሙከራዎች ባንመለከትም አዲስ ከተማ ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ፣ ቦዲቲዎች በመልሶ ማጥቃት ላይ አተኩረው ጥሩ ፉክክር ታይቶበታል። ጨዋታው በዚህ መልኩ ያለግብ የተጠናቀቀ ሲሆን የቦዲቲ ተጫዋቾች በጨዋታው መጠናቀቂያ ፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል በሚል ከጨዋታ አመራሮች ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡ ሲሆን በዚህም ሂደት ማቱሳላ የቀይ ካርድ ተመልክቷል።
በመቀጠል የተደረገው የነገላ አርሲ እና ቢሾፍቱ ከተማ ጨዋታ በነገሌ አርሲ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ ነገሌ አርሲዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ሲሆን ቢሾፍቱዎች በአንፃሩ በረጃጅም ኳሶች የጎል እድል ለመፍጠር ጥረት አድድገዋል። በዚህም ዘካርያስ ከበደ ከርቀት ያደረጋት መኩራ የመጀመርያ የጎል አጋጣሚ ነበረች።
ጎል በማስቆጠሩ አርሲዎች ቀዳሚ ሲሆኑ ምስጋና ሚኪያስ ከሳጥን ውጪ አክሮ የመታት ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ተለውጣ መሪ መሆን ችለዋል። በ41ኛው ደቂቃ ደግሞ ጎል አስቆጣሪው ምስጋና ያመቻቸለትን ኳስ ጀቤሳ ሚኤሳ አስቆጥሮ መሪነቱን አስፍቷል። ብዙም ሳይቆይ 44ኛው ደቂቃ ላይ በተጫዋቾች መካከል የተፈጠረውን እሰጥ አገባ ተከትሎ ጎል አስቆጣሪው ጀቤሳ ሚኤሳ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዶ የመጀመርያው አጋማሽ በነገሌ አርሲ 2-0 መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ቢሾፍቱዎች ያገኙትኝ የተጫዋች ብልጫ በመጠቀም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ የቻሉ ሲሆን በተለይ አብዱላዚዝ ዑመር በ61ኛ እና 66ኛ ደቂቃ ያደረጋቸውን ጠንካራ መከራዎች ግብ ጠባቂው አሸብር አምክኖባቸዋል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ አብዱላዚዝ ተሳክቶለት ግብ በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ቢችልም ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት ጨዋታው በነገሌ አርሲ 2-1 አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል።
ነገሌ አርሲ ድሉን ተከትሎ ከመሪው አርባምንጭ የነበረውን ልዩነት ወደ ሰባት መልሶ ማጥበብ ችሏል።
የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻ ወሳኝ የ 2-0 ድል ጋሞ ጨንቻ ላይ አስመዝግቧል።
በጨዋታው የተሻለ አጀማመር ማድረግ የቻሉት ጋሞ ጨንቻዎች በማቴዎስ ኤልያስ የግንባር ኳስ የጎል ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በመልሶ ማጥቃት ላይ አተኩረው ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ኮምቦልቻዎች በ25ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። ዮናታን ኃይሉ ያመቻቸለትን ኳስ ዮሐንስ ኪሮስ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት መቀየር ችሏል። ከጎሉ በኋላ ጨንቻዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ጫና ፈጥረው ቢጫወቱም ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳንመለከት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጋሞ ጨንቻዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በ66ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ያሬድ መኮንን ያደረገው ሙከራ እና በግብ ጠባቂ የተመለሰበት የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። ያገኙትን መሪነት ለማስጠበቅ ያለመ እንቅስቃሴ ያደረጉት ኮምቦልቻዎች በ79ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን አስተማማኝ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ማኑሄ ጌታቸው ከመስመር የተቀበለውን ኳስ በራሱ ጥረት ይዞ በመግባት ግብ ጠባቂውን አልፎ በማስቆጠር ጨዋታው በወሎ ኮምቦልቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ድሉ ለወሎ ኮምቦልቻ በሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ሆኖ ተመዝግባል።