ታክቲካዊ ትንታኔ ፡ ኢትዮጵያ ቡና 2-0 ደደቢት

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት መካከል ተካሂዶ አደገኞቹ 2-0 አሸንፈው ወደ ሊጉ አናት ተጠግቷል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ጨዋታውን እንዲህ ተመልክታዋለች፡፡

ቋሚ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና ( አሰልጣኝ – ጥላሁን መንገሻ )

ፌበርሲማ ኔልሰን

ዴቪድ በሻህ ፣ ሚልዮን በየነ ፣ ኤፍሬም ወንድወሰን ፣ አህመድ ረሺድ

ጋቶች ፓኖም ፣ ኤልያስ ማሞ

ሚከካኤል በየነ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ አስቻለው ግርማ

ቢንያም አሰፋ

ደደቢት ( አሰልጣኝ – ንጉሴ ደስታ )

ሲሳይ ባንጫ

ስዩም ተስፋዬ ፣ አከክሊሉ አየነው ፣ አዳሙ ሞሃመድ ፣ ብርሃኑ ቦጋለ

ሽመክት ጉግሳ ፣ ጋብሬል አህመድ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ታደለ መንገሻ

ሳሚ ሳኑሚ ፣ በረከት ይሳቅ

(ምስል 1)

Bunna 2-0 Dedebit (1)

ቅዳሜ 11፡30 ላይ በተጀመረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ባሸነፈበት ጨዋታ በቀይ ካርድ የተሰናበተው ጥላሁን ወልዴን በሚካኤል በየነ በመተካት ሲገባ ፣ በደደቢት በኩል በሲዳማ ቡና 2-0 ከተሸነፉበት ጨዋታ ዳዊት ፍቃዱን በበረከት ይሳቅ ፣ መስፍን ኪዳኔን በጋብሬል አህመድ ተክተው ገብተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና 4-2-3-1

ኢትዮጵያ ቡና በእለቱ ጨዋታ 4-2-3-1 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለመተግበር ሞክሯል፡፡ ጋቶች ፓኖም እና ኤልያስ ማሞ ሁለቱን ቦታ ሲይዙ ፣ ከሁለቱ ፊት ደግሞ ሚካኤል በየነ በግራ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ በመሃል እንዲሁም አስቻለው ግርማን በቀኝ መስመር አሰልፈዋል ፡፡ በብቸኛ አጥቂነት ደግሞ ቢንያም አሰፋ ተሰልፏል፡፡

እንደሚታወቀው ይህ አሰላለፍ ባለፉት ጥቂት አመታት የበላይ ሆኖ የቆየባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል

1ኛ. ከተከላካዮች ፊት የሚገኘውን ቦታ በተለምዶ በ1 ሆልዲንግ አማካይ ከመሸፈን ይልቅ በ2 ተጫዋቾች ለመሸፈን እና በተለይም የመስመር ተከላካዮች ከፊት ካሉት የመስመር አጥቂዎች ጋጋ ያለውን ሰፊ ክፍተት ለመሸፈን የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከፊት የሚገኙት 4 ተጫዋቾች (1 አጥቂ እና 3 አማካዮች) በነፃነት እንዲያጠቁ እድል ይሰጣቸዋል፡፡

በዚህ ጨዋታ ላይ ከሁለቱ አማካዮች አንደኛው የሆነው ጋቶች ፓኖም የግራ ፉልባኩ አህመድ ረሺድን ሲረዳ የነበረበት መንገድ ይህንን ያጠናክርልናል፡፡

2ኛ. የመሃል ሜዳ የበላይነትን ለመያዝ ይረዳል፡፡ በተለምዶ ከሚታየው የ3 መስመር አሰላለፍ (ተከላካይ ፣ አማካይ እና አጥቂ መስመር) ይልቅ ይህ አሰላለፍ ባለ 4 መስመር (4 band) በመሆኑ የማጥቃት አማራጮችን ለማስፋት ብሎም ከተጋጣሚ አማካዮች የቁጥር ብልጫን ለመውሰድ ያግዛል፡፡ በጨዋታው ከሁለቱ የደደቢት አማካዮች (ጋብሬል እና ሳምሶን) ውጪ ሁለቱ የመስመር አማካዮች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በላይኛው የሜዳ ክፍል የሚያሳልፉ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች የመሃል ሜዳውን ለመቆጣጠር አልተቸገሩም፡፡ በመሃል ሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ደደቢትን 4-2 ብልጫን ሲወስድ ነበር፡፡

ከዚህ ጋር ሊጠቀስ የሚገባው የዚህ አሰላለፍ ድክመት በሽግግር ወቅት በቡኑ ሲከላከል መቸገሩ ነው፡፡ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል ሲሸጋገር ከሁለቱ አማካዮቹ ውጪ ከፊት ያሉት የማጥቃት ባህርይ ያለቸው ተጫዋቾች በፍጥነት የቡድኑን የመከላከል ቅርፅ ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት አናሳ የሚሆን ከሆነና ተጋጣሚው የማጥቃት ሽግግር ፈጣን ከሆነ ቡድኑ ሊቸገር ይችላል፡፡

በጨዋታው ላይ ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው የደደቢት 4 ተጫዋቾች (ታደለ ፣ ሽመክት ፣ ሳሚ እና በረከት) አብዛኛውን ጊዜ በላይኛው የሜዳ ክፍል የሚያሳልፉ በመሆናቸው ኳስ በደደቢት እግር ስር በምትሆንበት ጊዜ ከኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች የቁጥር ብልጫን የሚወስዱበት አጋጣሚ ብዙ ነበር፡፡ (በተለይም በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች)

የደደቢት ወደ መሃል ሜዳ ተጠግቶ መከላከል

በፕሪሚየር ሊጉ የደደቢትን ያህል ወደ ፊት ተጠግቶ የሚከላከል ቡድን አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይህ አጨዋወት በትክክል ከተተገበረ ለቡድኑ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል፡፡ ተከላካዮቹ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረጉ እና በተከላካዮች እና በአማካዮች መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ ሰንጣቂ ኳሶችን እና የመቀባበያ አማራጮችን በማጥበብ ለመከላከል ማስቻሉ የሚጠቀሱ ጥንካሬዎች ሲሆኑ ግብ ጠባቂው ከፊቱ ከሚገኙት ተከላካዮች ጋር ያለውን ርቅት የማጥበብ ቅልጥፍናና በእግር የመጫወት ችሎታ ፣ የተከላካዮቹ የተጋጣሚ አጥቂዎችን ከጨዋታ ውጪ የማድረግ ጥበብ ጥሩ ካልሆነ እና የተጋጣሚው ቡድን ከተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍተተት ለመጠቀም የሚጥሩ ከሆነ ግን ቡድኑን ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡

በደደቢት ላይ የታየውም ይህ ነበር፡፡ ቡድኑ በተለይም ወደ መሃል ሜዳው ተጠግቶ መከላከሉ ከግብ ጠባቂው ጋር ያለውን ርቅት አስፍቶታል፡፡ በጨዋታው ለእንዲህ አይነት አጨዋወት ተስማሚ ያልሆነው ግብ ጠባቂው ሲሳይ ባንጫ እና ተከላካዮቹ መካከል የነበረው የመናበብ ችግር በጨዋታው ጎልቶ የወጣ ነበር፡፡ ይህም ከተከላካዮች ጀርባ ሩጫው በአስፈሪነቱ የሚታወቀው አስቻለው ግርማ በ39ኛው በአዳሙ ሞሃመድ እና ሲሲይ መካከል የተፈጠረውን ያለመናበብ ችግር ተጠቅሞ ለመጀመርያው ግብ መቆጠር ምክንያት ሆኗል፡፡

ከጎሉ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቡናው ኤልያስ ማሞ ለአስቻለው ግርማ የሚያሸግራቸው የተመጠኑ ኳሶች ደደቢት ላይ ተደጋጋሚ አደጋ እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ በ14ኛው ደቂቃ ዳዊት ከግራ መስመር ወደ ግቡ ያጠፈው ኳስ ፣ በ31ኛው ደቂቃ ኤልያስ ለአስቻለው ፣ አስቻለው ደግሞ ለቢንያም ያጠፈው ኳስ ፣ በ41ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ በተመሳሳይ ከኤልያስ የተሻገረለትን ኳስ አፈትልኮ በመውጣት አደጋ የፈጠረበት በ67ኛው ደቂቃ ቢንያም አሰፋ የቡናን 2ኛ ግብ ያስቆጠረበት አጋጣሚዎች ተመሳሳይነት የደደቢትን የአጨዋወት አተገባበር ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተተ ሆኗል፡፡ ( ምስል 2 )

Bunna 2-0 Dedebit (2)

 

ኤልያስ ማሞ እና ጋቶች ፓኖም

ሁለቱም አማካዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ አጨዋወታቸው ብስለት እየታከለበትና እየጎበተ መጥቷል፡፡ በእለቱ ጨዋታም ሁለቱ አማካዮች ድንቅ አቋም አሳይተዋል፡፡ ጋቶች ለመስመር ተከላካዮች ሽፋን በመስጠት ላይ የነበረው ግልጋሎት ድንቅ ነበር፡፡ በተለይም በመጀመርያዎቸ 20 ደቂቃዎች በሽመክት ፣ ስዩም አና በረከት ይሳቅ አማካኝነት ጫና በርክቶበት የዋለው አህመድ ረሺድን ሲረዳ እንዲሁም ቡናዎች ከማጥቃት ወደ መከላከል ሽግግር ወቅት በደደቢት አጥቂዎች የሚወሰደውን የቁጥር ብልጫ ለማመጣጠን (እንደ ሊቤሮ በመሆን) ያደረገው ጥረትም ጥሩ ነበር፡፡

ኤልያስ ማሞ በእለቱ ሁለት ሚናዎችን ሲወጣ ተስተውሏል፡፡ የመጀመርያው በጥልቅ አማካይ (Deep line Midfielder) ሚና የቡድኑን ፍሰት ሲቆጣጠር ጥሩ ነበር፡፡ በሁለተኝነት በጨዋታው ዳዊት እስጢፋኖስ ወደተለያዩ የሜዳው ክፍሎች እንቅስቃሴ ሲያደርግ ጥሎት የሚሄደውን ቦታ ተክቶ 10 ቁትር ላይ የሚገኝበት ጊዜም በርካታ ነበር፡፡ በጨዋታው ላይ አደጋ የሚፈጥሩ ኳሶችን ሲያሻግር የነበረውም በዚህ ቦታ ላይ እየተገኘ ነበር፡፡ ( ምስል 2 )

የተጫዋቾች ቅያሪ

በሁለተtኛው አጋማሽ (በተለይም ከ2ኛው ግብ መቆጠር በኋላ) የተደረጉት የተጫዋች ለውጦች የሁለቱንም አጨዋወት ለውጦታል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና አምበሉ ዳዊትን በዮናስ ገረመው እና በጨዋታው እምብዛም የነበረው ሚካኤል በየነን በተከላካይ አማካዩ ደረጄ ኃይሉ ቀይሮ ካስወጣ በኋላ በ4 የመሃል አማካዮች ዳይመንድ ቅርፅ በመስራት የደደቢተት የመሃል ለመሃል አጨዋወትን ለመስበርና የቁጥር ብልጫውንም ለመውሰድ ችሏል፡፡ (ምስል 3 ላይ በቡናማ ቀለም የተሰመሩትን መስመር ይመልከቱ)

በቡና ቅያሬ ምክንያት በመሃል ክፍሉ ክፍተት ያጡት ደደቢቶችም ኳስን በመያዝ ወደ ውስጥ ከመግባት ይልቅ በቀጥታ ኳስ ወደ መስመር በማውጣት ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ የተጫዋቾቹ ቅያሪም ይህንን የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ ከመስመር ወደ ውስጥ ሰብሮ የሚገባው ታደለን ቀጥተኛ የመስመር አማካይ በሆነው ሄኖክ ኢሳይያስ ቀይረው ሲያስወጡት ወደ መስመር እና አማካይ መስመር እየወጣ ኳስ ለማግኘት ጥረት የሚያደርገው በረከት ይሳቅን የሳጥን አጥቂ በሆነው ዳዊት ፍቃዱ ቀይረው አስወጥተዋል፡፡ ይህም የደደቢትን አጨዋወት ወደ ባህላዊ 4-4-2 (በሁለት ቀጥተኛ የመስመር አማካዮች እና በ2 ተመሳሳይ የሳጥን ውስጥ አጥቂዎች) ወስዶታል፡፡

(ምስል 3 ላይ በሰማያዊ የተሰመሩት መስመሮችን ይመልከቱ)

Bunna 2-0 Dedebit (3)

ያጋሩ