አንድ ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በተደረገበት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ በተመስገን በጅሮንድ ግብ ወላይታ ድቻን 1-0 ረቷል።
በ20ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ በ19ኛው ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር የነበራቸው ጠዋታ በአለልኝ አዘነ ሞት ምክንያት የባህር ዳር ጨዋታ ስለተራዘመ የጨዋታ ሳምንቱ ያለፋቸው ሠራተኞቹ በ18ኛው ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ራምኬል ሎክ በተስፋዬ መላኩ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ፉዓድ አብደላ ተተክተው ገብተዋል። የጦና ንቦቹ በአንጻሩ በ19ኛው ሳምንት በመቻል 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ፍጹም ግርማ እና ዘላለም አባተን አስወጥተው አናጋው ባደግ እና ጸጋዬ ብርሃኑን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል።
ቀን 10፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያ በመስጠት ለመጫወት ሲሞክሩ 13ኛው ደቂቃ ላይ የድቻው ብሥራት በቀለ ከቀኝ መስመር 41ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አብነት ደምሴ ከግራ መስመር በተሻገሩላቸው እና በግንባር ገጭተው ካደረጓቸው ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ የግብ ዕድሎችም ሆኑ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች አልታዩም ነበር። ሆኖም 25ኛው ደቂቃ ላይ የድቻው ሀብታሙ ቦጋለ በጉዳት ምክንያት በአዛሪያስ አቤል ሊቀየር መገደዱ ብቻ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር።
ከዕረፍት መልስም ጨዋታው እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ተቀዛቅዞ ሲቀጠል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግበት ቀጥሎ 78ኛው ደቂቃ ላይ በሠራተኞቹ አማካኝነት በተደረገው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ ተቆጥሯል። ሄኖክ ኢሳይያስ ተቀይሮ ከገባው ፉዓድ አብደላ በተቀበለው ኳስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተመስገን በጅሮንድ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ባደረጓቸው ቅያሪዎች በተለይም በሙሉዓለም መስፍን እና ፉዓድ አብደላ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለው በተደጋጋሚ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ከጨዋታ ጨዋታ እየተቀዛቀዙ የሄዱት ወላይታ ድቻዎች በአንጻሩ ተደራጅተው ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ተቸግረው ይባስ ብሎም 90+4ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ናሴሮን በሁለት ቢጫ ካርድ አጥተዋል። ጨዋታውም በወልቂጤ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም ለሠራተኞቹ ከ11 ጨዋታዎች በኋላ የተገኘ ሆኗል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የጎል ዕድል መፍጠር እንዳልቻሉ ጠቁመው ከዕረፍት መልስ ማጥቃትን አስበው ያደረጉት ቅያሪ ውጤታማ እንዳልነበር እና የፊት መስመራቸው ላይ መሳሳት እንዳለ ሲናገሩ ድል የቀናቸው የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በበኩላቸው ተጫዋቾቹ ላይ ካለው ጫና አንጻር ድሉ እጅግ አስደሳች መሆኑን ተናግረው የአምስት ወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው በመጠቆም ክለቡ ደመወዝ ቢከፍል ለውጤታቸው ማማር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።