በሀያኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ
በነገው ዕለት ከሚደረጉ ሁለት መርሐ-ግብሮች መካከል ቀዳሚ የሆነውና በአራት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኘውን ተጠባቂ ጨዋታ 10:00 ላይ ይጀምራል።
ከአስደናቂው ግስጋሴ በኋላ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ የጣሉት ቡናማዎቹ በሰላሣ ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ከባድ የሚባሉ መርሃ ግብሮች ያከናወኑት ቡናማዎቹ ከፋሲል ከነማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ መጠነኛ መሻሻሎች ቢያሳዩም በጥሩ ግስጋሴ በነበሩበት ወቅት ያሳዩት የብቃት ደረጃ መድገም አልቻሉም። በተለይም በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግቡን ሳያስደፍር ከቆየ በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ወደ ቀደመው ወጥነት ያለው ድንቅ ብቃቱ መመለስ ይኖርበታል። በነገው ዕለትም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስቆጠረ የኃይቆቹ ስል የፊት መስመር መቋቋም የሚችል ብቃት ላይ መገኘት ግድ ይላቸዋል።
ፈጣን በሚባል ጊዜ በጎ ለውጥ ማምጣት የቻሉት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በሁለተኛው ዙር የታየባቸው ውስን መቀዛቀዝ ቶሎ ፈተው ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ከዚህ መርሀ ግብር ሙሉ ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። አሰልጣኙ ቅድምያ የመከላከል አደረጃጀቱ የሚደረግ ለውጥ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከተከታታይ ጨዋታዎች ድንቅ እንቅስቃሴ በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመርም ውስን ለውጥ ይደረግበታል ተብሎ ይታመናል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አስፈሪ የፊት መስመር ጥምረት የገነቡት ኃይቆቹ የመልሶ ማጥቃትና ቀጥተኛ አጨዋወታቸው ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል። የማጥቃቱም ሆነ የተከላካይ ክፍሉ ለማሻሻል በወሰናቸው ቁልፍ ውሳኔዎች ለውጥ ያመጡት አሰልጣኝ ዘርአይ ቡድን ላይ ውስን የወጥነት ችግር ቢታይም በጥቅሉ ሲታይ ግን በሂደት ጥሩ ቡድን እንደገነቡ መካድ አይቻልም።
ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ስምንት ግቦችና በተከታታይ ጨዋታዎች የሰበሰባቸው ነጥቦችም የመሻሻሉ ማሳያዎች ናቸው። በነገው ተጠባቂ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘትም በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ የሚሉበት ዕድል ሊፈጥርላቸው ስለሚችል ላለፉት ሦስት ሳምንታት ያስመዘገቡት ጥሩ ውጤት ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።
የቡድን ዜናዎችን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ጫላ ተሺታ እና መሐመድኑር ናስር በጉዳት ነገም እንደማይኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን የኃይለሚካኤል አደፍርስ መድረስም አጠራጣሪ ነው። ሀዋሳ ከተማዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በአንፃሩ በመጨረሻው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት ያልተሳተፈው እንየው ካሳሁን ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።
ከሊጉ የተሳትፎ ዝርዝር ጠፍተው የማያውቁት ክለቦቹ ነገ ለ50ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። በጨዋታዎቹ ሁለቱም ዕኩል 16 ጊዜ ድል ሲያደርጉ 17 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 58 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 52 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።
ፋሲል ከነማ ከ ድሬድዋ ከተማ
ከሁለት ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገቡትን ቡድኖች የሚያገናኘው ነገ ምሽት 01:00 ላይ ይከናወናል።
በመጨረሻዎቹ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ከአንድ ነጥብ በላይ ማሳካት ያልቻሉት ፋሲል ከነማዎች በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ባለው ፉክክር ለመሰንበት ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይፈልጋሉ። በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ ወደ መሪዎቹ የመጠጋት ዕድላቸውን ያባከኑት ዐፄዎቹ የነገው ጨዋታ የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል ከሚያደርጉት የእርሰበርስ ጨዋታ በፊት የሚደረግ በመሆኑ የዚህን ጨዋታ ዋጋ ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል። ዐፄዎቹ ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ቀንሰው አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ከአራት እስከ ሰባት ባለው ደረጃ ላይ ከሚታየው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ተጨማሪ ነጥብ መጣል ወደ ኋላ ሊጎትታቸው ሰለሚችል ለጨዋታው ከፍ ያለ ትርጉም መስጠታቸው አይቀርም።
በተመሳሳይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከድል ጋር ከተራራቀው ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት የነገው ወሳኝ ጨዋታም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች በማስቆጠር በጥሩ ብቃት የሚገኘው የቡድኑ የፊት መስመር ተጋጣሚው በቅርብ ሳምንታት ጠንካራ የተከላካይ ክፍል የገነባ እንደመሆኑ ጥንካሬውን ማስቀጠል ይኖርበታል።
ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የናፈቀውን ድል አግኝቶ ነጥብ እና ደረጃውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባል። ለሳምንታት ከዘለቀው ጥሩ ብቃት በኋላ በተከታታይ ነጥብ የጣሉት ብርቱካናማዎቹ ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው ካቀና በኋላ ውስን መቀዛቀዝ አሳይተዋል።
በ19ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አቻ የተለያየው ቡድኑ በዕለቱ እንደ ወትሮ የተጋጣሚውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመግታት የተዋጣለት ቀን ቢያሳልፍም በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው መቀዛቀዝ ግን ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዞ እንዳይወጣ አድጎታል። በመጀመርያው አጋማሽ የተጋጣሚን ጥቃት በብቃት ከመመከት አልፈው ጨዋታው ለመቆጣጠርም ጥረት ያደረጉት ብርቱካናማዎቹ በጨዋታው ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ክፍተት ተስተውሎባቸዋል።
በተለይም ከተከላካይ መስመር እየተነሱ እንዲያጠቁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበረው ዓብዱለጢፍ መሐመድ እና ዳግማዊ ዓባይ ተከላካዮችን በመረበሽ የተዋጣለት ጊዜ ቢያሳልፉም የግል እንቅስቃሴያቸው በቡድን የታጀበ አለመሆኑ እንደሚፈለገው ውጤታማ መሆን አልቻሉም። ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በዝቶ ለመግባት የማይደፍረው የቡድኑ የመሀል ክፍል ያለው የተገደበ እንቅስቃሴም የመስመር አጨዋወቱ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል። ቡድኑ በነገው ጨዋታ ወሳኙ አጥቂ ቻርለስ ሙሴጌ በጉዳት ማጣቱም የፊት መስመሩ እንዳያሳሳው ያሰጋል። ከዚህ በተጨማሪ የነገ ተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ የግብ ዕድሎችን በቀላሉ የማይፈቅድ ስለሆነ የሚገኙ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም የግድ ይላቸዋል።
በጨዋታው የፋሲል ከነማዎቹ አፍቅሮት ሰለሞን እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን የጌታነህ ከበደ ፣ አምሳሉ ጥላሁን እና ዓለምብርሃን ይግዛው መሰለፍ አጠራጣሪ ነው። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ በመጨረሻው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ የወጣው ቻርለስ ሙሴጌ እና ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ያሉት ተመስገን ደረስ ፣ ያሲን ጀማል እና አብዱልፈታህ ዓሊ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።
ፋሲል እና ድሬዳዋ በሊጉ እስካሁን 13 ጊዜ ተገናኝተዋል። በዚህም ዕኩል አምስት ድሎችን ሲያሳኩ በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ 30 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ 18 ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 12 ጎሎች አስመዝግበዋል።