ብርቱካናማዎቹ ከመመራት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች ፋሲል ከነማን 2ለ1 አሸንፈዋል።
በምሽቱ መርሐግብር ፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ሲገናኙ ዐፄዎቹ በ19ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1ለ1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አዲስ ፈራሚው ሀቢብ መሐመድ ፣ ኤልያስ ማሞ እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በመናፍ ዐዎል ፣ አቤል እንዳለ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ተተክተው ገብተዋል። ብርቱካናማዎቹ በአንጻሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 1ለ1 ከተለያዩበት አሰላለፍ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ ጉዳት ላይ በሚገኘው ቻርለስ ሙሴጌ ምትክ ከቅጣት የተመለሰው ኤልያስ አህመድ ተተክቷል።
ምሽት 1 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ድሬዎች በረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያ ሰጥተው መጫወት የቻሉት ፋሲሎች በአንጻሩ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ 7ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለሙ የግንባር ኳስ አድርገዋል።
በቁጥር እየበዙ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መታተር የጀመሩት ዐፄዎቹ 13ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቃልኪዳን ዘላለም በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው የመሃል ተከላካዩ ምኞት ደበበ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ዋና አጥቂያቸውን ቻርለስ ሙሴጌን ዛሬ በጉዳት መጠቀም ያልቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች የፊት መስመራቸው ሳስቶ የታየ ሲሆን የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ 34ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። በዚህም ኢያሱ ለገሰ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ዘርዓይ ገብረሥላሴ ዓየር ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ ይዞበታል።
በመጠኑ ቀዝቃዛ የነበረው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ሁለት ደቂቃዎች ውስጥ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማዎች ተጨማሪ ወርቃማ የግብ ዕድል ፈጥረው ቃልኪዳን ዘላለም ከሽመክት ጉግሳ የተቀበለውን ኳስ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ያደረገውን ሙከራ ሄኖክ ሀሰን በግሩም ሸርታቴ አግዶበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተጋግሎ ሲቀጥል ካርሎስ ዳምጠውን በኤልያስ አህመድ ቀይረው ያስገቡት ብርቱካናማዎቹ 51ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ሚኬል ሳማኪ ሲያስወጣባቸው በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ዐፄዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ቃልኪዳን ዘላለም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።
በፈጣን ሽግግሮች ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ድሬዳዋዎች 58ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ዕድል ፈጥረው ሱራፌል ጌታቸው በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ተከላካዮችን በግሩም ክህሎት አታልሎ በማለፍ ወደ ውሰጥ ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያቋርጥበት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ በፋሲል ከነማ በኩል ቃልኪዳን ዘላለም በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ምኞት ደበበ ከነካው በኋላ ያገኘው ተከላካዩ ሀቢብ መሐመድ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩሌ ተቀይሮ ገብቶ ጎልቶ የሚታይ ልዩነት መፍጠር የቻለው ካርሎስ ዳምጠው 64ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ ተጭኖ በቀማው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ተከላካዩ ሀቢብ መሐመድ ቢመልስበትም 73ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሱራፌል ጌታቸው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በግንባር ገጭቶት ኳሱ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ መረቡ ላይ አርፏል።
ፋሲል ከነማዎች ባልተረጋጋ እንቅስቃሴ የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት ሽግግር ለመመከት ሲቸገሩ 76ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። መሐመድ አብዱለጢፍ ከግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ኢስማኤል አብዱልጋኒዮ የግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ ድክመት ተጨምሮበት በግንባሩ በመግጨት ብርቱካናማዎቹን መሪ ያደረገች ግብ ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።
በርካታ ቅያሪዎችን በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች 83ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ማስረሻ በግሩም ክህሎት በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት በመግባት ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው አብሮት ተቀይሮ የገባው ጃቢር ሙሉ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዐብዩ ካሣዬ በግሩም ቅልጥፍና አግዶበታል።
ለተመልካች ሳቢ በነበሩት የመጨረሻ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች ውጤቱን ይዘው ለመውጣት የተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት መከተልን ሲመርጡ ፋሲል ከነማዎች በአንጻሩ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ጥረት በማድረግ 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ የገባው ዓለምብርሃን ይግዛው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ናትናኤል ማስረሻ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሣዬ በቀላሉ ይዞበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ የ2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ እንደነበሩ በመናገር ለተጋጣሚያቸው በሚሆን አቀራረብ ለመቅረብ መገደዳቸውን ገልጸው ቀጣይ ጨዋታዎችንም ለማሸነፍ እንደሚሠሩ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ ጠቁመው በሁለተኛው አጋማሽ በቡድናቸው ላይ የታየው ማፈግፈግ ለተጋጣሚያቸው መነሳሻ እንደሆነ እና ዋጋም እንዳስከፈላቸው በመናገር የተጫዋቾች ጉዳት በመጠኑ ክፍተት እንደፈጠረባቸው ሀሳባቸውን ስጥተዋል።