በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ዕለት የሚካሄዱ ሁለት መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ አዳማ ከተማ
ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ 10 ሰዓት ላይ ይጀምራል።
ከተከታታይ ሁለት አቻዎች በኋላ ሀምበርቾን ሁለት ለምንም አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። ባለፉት አስራ ሰባት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ያላስተናገዱት ነብሮቹ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች መረባቸውን ባለማስደፈር የወትሮው ጥንካሬያቸው ማስቀጠል ችለዋል። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት የታየበትን የግብ ማስቆጠር ድክመት በመጨረሻው ጨዋታ መፍታት ቢችልም ለነገው ተጋጣሚው የመከላከል ጥንካሬ የሚፈትን ሚዛናዊ አቀራረብ ይዞ መምጣት ይኖርበታል። ከዚ ቀደም በርካታ ግቦች ሲያስተናግዱ የነበሩት አዳማዎች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት መገንባት ችለዋል፤ አራት ግቦች ከተቆጠረባቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ወዲህ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ያሳዩት እንቅስቃሴና ያስተናገዱት የግብ መጠንም የዚ ማሳያ ነው። ነብሮቹ ጠንካራው የአዳማ የፊት መስመር እንቅስቃሴ መግታትም ዋነኛ እቅዳቸው እንደሚሆን እሙን ነው። ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ግን የፊት መስመራቸው ከወትሮው በተለየ ጥንካሬ መገኘት ይኖርበታል።
በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ የሚገቡት አዳማ ከተማዎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻሉ ቢያንስ አንድ ደረጃ ማሻሻል ይችላሉ። አዳማ ከተማዎች በመሀል ካጋጠማቸው አንድ ሽንፈት ውጭ ባለፉት አስር ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገዱም ፤ በተለይም ከወሳኙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ድል በኋላ በተሻለ የማሸነፍ ስነልቦና ላይ እንዳሉ ይታመናል። በመጨረሻው የሊግ ጨዋታቸው ላይ ውስን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው አዳማዎች በነገው ጨዋታ መሰል ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም ባለፉት ሁለት መርሐግብሮች አምስት ግቦች ማስቆጠር የቻለው የቡድኑ የፊት መስመር ግን ከባድ ፈተና ከፊቱ አለ። ዕድሎች ለመፍጠር እምብዛም የማይቸገረው ቡድኑ በነገው ዕለት በቀላሉ ሰፊ የማጥቂያ ክፍተቶች ያገኛል ተብሎ አይገመትም። ወደ ራሱ የግብ ክልል ቀርቦና ጥቅጥቅ ብሎ ለመጫወት የሚመርጠውን ቡድን ለማስከፈትም ትዕግስት የተሞላበት ቅብብል ከማድረግ ባለፈ የሚገኙትን ዕድሎች በአግባቡ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል።
በጨዋታውም በፈጣን ተጫዋቾች የተገነባው የአዳማ የፊት መስመር እና እንደ ቡድን የተዋቀረው የሀዲያ ሆሳዕና የመከላከል አደረጃጀት የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።
በሀዲያ ሆሳዕና በኩል መለሠ ሚሻሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ግርማ በቀለ ግን ከጉዳቱ ተመልሷል። በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ መስዑድ መሀመድ መጠነኛ ህመም ያጋጠመው ሲሆን ቢኒያም ዐይተን ደግሞ በአምስት ቢጫ ካርድ መነሻነት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል።
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን
ከአደገኛው ቀጠና ለመራቅ የሚያልሙ ሁለት ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ነው።
በሃያ ሦስት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ወርቃማ ዕድል አግኝተዋል። ሲዳማዎች ባለፉት ሦስት መርሀ ግብሮች ሽንፈት ባለማስተናገድ አምስት ነጥቦች መሰብሰብ ቢችሉም ደረጃቸውን ማሻሻል አልቻሉም፤ አሁን ግን ወላይታ ድቻ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ደረጃቸውን የማሻሻል ዕድል በእጃቸውን ላይ አለ። ባለፉት ሳምንታት ከባድ ጨዋታዎች ያከናወኑት ሲዳማ ቡናዎች በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የሚገኙ አምስት ክለቦችን በተከታታይ መግጠማቸው ደረጃቸው እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል። ቡድኑ በተጠቀሱት መርሐግብሮች የሰበሰበው ውድ አራት ነጥቦችም በቅርብ ሳምንታት ቡድኑ ያሳካው ትልቁ ነገር ነው። በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣትም ደረጃውን ከማሻሻል አልፎ ከታች ከሚገኘው የቅርብ ተፎካካሪው ያለው የነጥብ ልዩነት የሚያሰፋ እንደመሆኑ መርሐግብሩ ወሳኝ ነው።
በብዙ መለኪያዎች ተሻሽለው የቀረቡት መድኖች የቅርብ ሳምንታት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴያቸውን በውጤት ለማጀብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። የማጥቃት አጨዋወታቸውን ለማሻሻል በወሰዷቸው እርምጃዎች ውስን ለውጦች ያመጡት መድኖች በሁለቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች አራት ግቦች ማስቆጠር ችለዋል። ሆኖም ለስህተቶች ተጋላጭ የሆነውና ባለፉት ሦስት መርሐግብሮች በየ ጨዋታው ሁለት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት መሰረታዊ ለውጦች ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ በጥሩ የለውጥ ሂደት ላይ ያለው የፊት መስመር ውጤታማነቱን ማስቀጠል ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል አማካዩቹ ሀይደር ሸረፋ እና ንጋቱ ገ/ሥላሴ በጉዳት እንዲሁም ብሩክ ሙሉጌታና አብዲሳ ጀማል በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። ሲዳማ ቡናዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።