ሀዲያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ አዳማ ከተማን በመርታት በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ከ አዳማ ከተማ ተገናኝተው ነብሮቹ በ19ኛው ሳምንት ሀምበርቾን 2ለ0 ከረቱበት አሰላለፍ ሳሙኤል ዮሐንስን አሳርፈው አዲስ ፈራሚውን ዑመድ ኡክሪን ሲያስገቡ አዳማዎችም በተመሳሳይ ጊዮርጊስን 2ለ1 ካሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ በአምስት ቢጫ ካርዶች ቅጣት ላይ በሚገኘው ቢኒያም ዐይተን ምትክ ነቢል ኑሪ በቋሚ አሰላለፍ ተካቷል።
በዝናብ ታጅቦ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ5ኛው ደቂቃ መሪ ሊያገኝ ነበር። በዚህም የአዳማ ከተማው አምበል መስዑድ መሐመድ በኳስ ቅብብል ወቅት የተሳሳተውን ኳስ የተረከበው የሀዲያው አምበል ዳዋ ሁቴሳ ከርቀት አክርሮ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ ሊያደርግ ቢጥርም ሰዒድ ጥብቁን ኳስ እንደ ምንም አምክኖታል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት የወጡት አዳማዎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በቦና ዓሊ አማካኝነት ታፔ አልዛየርን ለመፈተን ሞክረዋል።
ጥሩ ፉክክር እያስመለከተ የሚገኘው ጨዋታው በ17ኛው ደቂቃ በድንቅ የቅጣት ምት በተቆጠረ ጎል አዳማን መሪ አድርጓል። በሩብ ሰዓት ተከላካዩ ቃለዓብ ሙሴ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የፍፁም ቅጣት ምት መግቢያው ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ መሬት ለመሬት በመምታት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። መመራት የጀመሩት ሀዲያዎች ከቆመ ኳስ ለተቆጠረባቸው ጎል ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከሌላ የቆመ ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር። በዚህም ከመዓዘን የተሻማውን ኳስ ከድር ኩሊባሊ ወደ ጎልነት ለመቀየር ጥረት ቢያደርግም ሰዒድ ውጥኑን አክሽፎበታል።
በእንቅስቃሴ እያደረጉ የመጡት ሀዲያዎች ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር ቀላል አልሆነላቸውም። በአንፃሩ ጨዋታውን በመቆጣጠር ረገድ የተሻሉት አዳማዎች በ33ኛው ደቂቃ ነቢል ዮሴፍ እና መስዑድ በጥሩ መናበብ የተቀባበሉትን የመጨረሻ ኳስ አግኝቶ በመሞከር ሁለተኛ ግብ ሊያስቆጥር ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው 5 ደቂቃ መገባደጃ ላይ ሀዲያዎች ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ አቻ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ተመስገን ከግራ መስመር የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ዳዋ አግኝቶ መዳረሻውን መረብ አድርጎታል። አጋማሹም አንድ አቻ ተፈፅሟል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሀዲያዎች እጅግ የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረው ሳይጠቀሙበት በቀሩት ሁነት የጀመረ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ነብሮቹ ሌላ ግልፅ አጋጣሚ ቢፈጥሩም ያሰቡትን መሪነት ማግኘት አልቻሉም። በ56ኛው ደቂቃ ዳግም ወደ መሪነት ለመሸጋገር የጣሩት አዳማዎች የጨዋታውን እጅግ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በዚህም ቦና ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘበትን አጋጣሚ ከመሐል በተላከ ኳስ አግኝቶ በወረደ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአጋጣሚው የግብ ዘቡ ታፔ ሰውነቱን አግዝፎ በጥሩ የሰዓት አጠባበቅ ኳሱ ወደ ጀርባው እንዳያልፍ ያደረገበት ውሳኔ ሀዲያን በጨዋታው ያቆየ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ዑመድን ቀይሮ የገባው ሳሙኤል ዮሀንስ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ የነበረ ሲሆን በ59ኛው ደቂቃም ከርቀት መልካም የሚባል ምት ወደ ሰዒድ ግብ ልኮ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም የግቡ ባለቤት ዳዋ ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ቢዳዳም ግብ ጠባቂው አልፈቀደለትም።
በአቻ ውጤት የቀጠለው ፍልሚያው 78ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግዷል። በዚህም የአዳማ ከተማው ተከላካይ ታዬ የቆመ ኳስ በሚሻማበት ወቅት ከኳስ ውጪ ያልተገባ አጨዋወት ተጫውቷል በሚል ከዕለቱ አልቢትር ኃይለየሱስ ቀይ ካርድ ተመልክቷል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በሙከራዎች ረገድ ሻል ያሉት ሀዲያዎች የቁጥር ብልጫ ካገኙ በኋላ ይበልጥ የአዳማ የግብ ክልል ለመጎብኘት ተመላልሰዋል። በዚህም በ83ኛው ደቂቃ ውጥናቸው ሰምሮ መሪ ሆነዋል። የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው ዳዋ በዚህ ደቂቃ እጅግ ምርጥ ተንጠልጣይ ኳስ ለብሩክ ማርቆስ አቀብሎት ብሩክ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 2ለ1 ተጠናቋል።
ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ድሉን ያገኙት የሀዲያ ሆሳዕናው አሠልጣኝ ግርማ ታደሠ የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ተንተርሰው ባደረጉት አጨዋወት ድሉን እንዳገኙ አውስተው በሚፈልጉት መልኩ እንደተጫወቱ በመጥቀስ ለማሸነፋቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠሩት ጎል ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ አብራርተዋል። የአዳማ ከተማው አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው በማንሳት በቀይ ካርዱ የዳኛውን ውሳኔ እንደሚያከብሩ አመላክተው በቀጣይ ዛሬ የሰሯቸውን ስህተቶች አሻሽለው እንደሚመጡ ተናግረዋል።