በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድን እና ሲዳማ ቡና ያለ ግብ ተለያይተዋል።
በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን ተገናኝተው ሲዳማዎች በ19ኛው ሳምንት ሻሸመኔን 1ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አበባየሁ ዮሐንስ ፣ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን ፣ በዛብህ መለዮ ፣ ቡልቻ ሹራ እና ማይክል ኪፖሩል ወጥተው ጊት ጋትኩት ፣ ደግፌ ዓለሙ ፣ ኢማኑኤል ላርዬ ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ ተተክተው ገብተዋል። መድኖች በአንጻሩ ከሀዋሳ ከተማ ጋር 2ለ2 ከተለያዩበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ከ49 ጨዋታዎች በኋላ በአዲሱ ፈራሚ ተክለማርያም ሻንቆ ተተክቶ ወደ ተጠባባቂ ወንበር ሲወርድ በአምስት ቢጫዎች ቅጣት ላይ የሚገኘው ብሩክ ሙሉጌታ በመሐመድ አበራ ተተክቷል።
ምሽት 1 ሰዓት ሲል በደረጃው ግርጌ በሚፈጥረው ልዩነት ትልቅ ትርጉም ይዞ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ፉክክር ማድረግ ችለዋል። የመጀመሪያው ሙከራም በመድኑ መሐመድ አበራ አማካኝነት ተደርጎ የመስመር አጥቂው ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ አስወጥቶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም የሲዳማው ኢማኑኤል ላርዬ ከሳጥን አጠገብ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ይዞበታል።
በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል የመድረስ ፍላጎት እየታየበት በቀጠለው ጨዋታ መድኖች 16ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ወገኔ ገዛኸኝ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ጄሮም ፊሊፕ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ እና የግቡ የቀኝ ቋሚ ግብ እንዳያስቆጥር ከልክለውታል። ሲዳማዎች በአንጻሩ በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን 34ኛ ደቂቃ ላይ ፈጥረው ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ በተከላካይ ከተመለሰ በኋላ ያገኘው ጊት ጋትኩት በኃይል ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ኢትዮጵያ መድኖች 37ኛው ደቂቃ ላይ በያሬድ ካሳዬ አማካኝነት ከቅጣት ምት ሙከራ አድርገው በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ሲወጣባቸው 45+3ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ያሬድ ካሳዬ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጄሮም ፊሊፕ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስም የመሃል ተከላካይ ቦታ ላይ ሰዒድ ሀሰንን አስወጥተው በርናንድ ኦቼንግን በማስገባት እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በጥሩ ግለት የጀመሩት መድኖች 49ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ አበራ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ በተቆጣጠረው ኳስ አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል። በአስር ደቂቃዎች ልዩነትም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ያሬድ ካሳዬ በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ሳይዘጋጅ ያገኘው ሚሊዮን ሰለሞን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
እየተቀዛቀዘ በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች 76ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድል አግኝተው መሐመድ አበራ ሳጥን ውስጥ ባገኘው ኳስ ደግፌ ዓለሙን በማለፍ ያደረገው ሙከራ ግብ ጠባቂውን መፈተን ሳይችል ሲቀር በስድስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ አለን ካይዋ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ መክብብ ደገፉ ኳሱን አግዶበት ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት የተቸገሩት ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻ ደቂቃዎች በመጠኑ በመነቃቃት 85ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹን የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረው ማይክል ኪፖሩል ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብርሃኑ በቀለ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በጨዋታው ደስተኛ እንደነበሩ በመጠቆም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ውስንነት እንደነበረባቸው ሆኖም የመከላከል አደረጃጀታቸው ጠንካራ እንደነበር ሲናገሩ የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በበኩላቸው ውጤቱ ለእነሱ ጥሩ እንዳልነበር ተናግረው እንደ ፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች ማሸነፍ ይጠበቅባቸው እንደነበር በመጠቆም አጨራረስ ላይ ያለባቸው ድክመት ከድል ጋር እንዳይታረቁ ምክንያት እንደሆነባቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።