የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በመመርኮዝ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።
አደራደር 4-3-3
ግብ ጠባቂ
መክብብ ደገፉ – ሲዳማ ቡና
ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ ተጋርቶ በወጣበት ጨዋታ ቡድኑ ላገኛት አንድ ነጥብ የግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ የግብ አጠበባበቅ ብቃት ጥሩ ነበር። ለግብ የቀረቡ ጥርት ያሉ አራት ኳሶችን በጥሩ ቅልጥፍና ከማዳኑ በተጨማሪ ከማዕዘን ምት ሆነ ከሌሎች አቅጣጫዎች የሚሻሙ ኳሶችን ጊዜውን ጠብቆ የሚቆጣጠርበት ሁኔታ እና ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በጥሩ ውሳኔ ሂደቱን በመጠበቅ በፍጥነት ወጥቶ የሚቆጣጠርበት መንገድ በሶከር ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ለተከታታይ ሳምንታት እንዲመረጥ አስችሎታል።
ተከላካዮች
በረከት ወልደዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና
የነብሮቹ የቀኝ መስመር ተከላካይ በረከት በቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ ላይ ያለው ድርሻ እያደገ ይገኛል። ቡድኑ አዳማ ከተማን ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ በማስቻሉ የነበረው ብቃት መልካም የሚባል ነበር። ዋና ኃላፊነቱ መከላከል ቢሆንም ለማጥቃት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመሄድ የማይደክመው ተጫዋቹ የመጨረሻ ኳሶቹ ውጤታማ ባይሆኑም ባሳየው ጥሩ የሜዳ ላይ ቆይታ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ለመካተት ችሏል።
ፍሬዘር ካሳ – ባህር ዳር ከተማ
የቡድን አጋራቸው አለልኝ አዘነን ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ በከፍተኛ ሀዘን ስሜት ሆነው የቡድኑ አባላት ይህን ጨዋታ በማሸነፍ እና የእርሱ መታሰቢያ በማድረጉ ረገድ ውጤታማ እንዲሆኑ የኋላው ደጀን ፍሬዘር ካሳ አበርክቶ ከፍ ያለ ነበር። ሻሸመኔዎች በረጅሙ አጥቂዎቻቸውን የሚፈልጉ ኳሶችን በመጣል በተደጋጋሚ የባህር ዳር የግብ ክልል ለመረበሽ ቢሞክሩም የመሐል ተከላካዩ ፍሬዘር በጥሩ ንቃት የሚጣሉ ኳሶችን አደጋ እንዳይፈጥሩ በማድረግ ጥሩ ቀንን በማሳለፉ በምርጥ አስራ አንድ ውስጥ እንዲካተት ሆኗል።
ኢያሱ ለገሠ – ድሬዳዋ ከተማ
ድሬዳዋ ከተማዎች ከመመራት ተነስተው ፋሲል ከነማን 2ለ1 ሲያሸንፉ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከሉ ረገድ ሥራ በዝቶባቸው ሲያሳልፉ የመሃል ተከላካዩ ኢያሱ በግሩም ቅልጥፍና በሚወርዳቸው ጊዜያቸውን የጠበቁ ሸርተቴዎች ውጤት ቀያሪ ሊሆኑ የሚችሉ የነበር ሲሆን በአንድ አጋጣሚም ዘርዓይ ገብረሥላሴ አይጠቀምበት እንጂ ወርቃማ የግብ ዕድል መፍጠር ችሎ ነበር።
ሄኖክ ኢሳይያስ – ወልቂጤ ከተማ
ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ያሳካው ባለ ብዙ ልምዱ የግራ መስመር ተከላካይ ሄኖክ ኢሳይያስ ሠራተኞቹ ከአስራ አንድ ጨዋታ በኋላ ከድል ጋር እንዲታረቁ በማስቻል የነበረው አስተዋፆኦ ከፍ ያለ ነበር። በዋናነት የመከላከል ሥራው ላይ ትኩረት አድርጎ የዋለው ሄኖክ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደፊት በመሄድ የሚጥላቸው ኳሶች አደጋ ያደርሱ ነበር። በዚህም ሂደት በ78ኛው ደቂቃ ለተገኘችው የማሸነፍያ ብቸኛ ጎል በእርሱ ተሻጋሪ ኳስ ነበር ተመስገን በጅሮንድ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ ያሳረፈው።
አማካዮች
ብሩክ ማርቆስ – ሀዲያ ሆሳዕና
ነብሮቹ ከመመራት ተነስተው አዳማ ከተማን 2ለ1 ሲያሸንፉ አማካዩ እጅግ ስኬታማ ቀን አሳልፏል። ከጨዋታ ጨዋታ ተፅዕኖው ከፍ እያለ የመጣው አይደክሜው ብሩክ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቁ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይልቁንም ከዳዋ ሆቴሳ የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ በመቆጣጠር የቡድኑን የማሸነፊያ ግብም ከሳጥን አጠገብ በአስደናቂ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።
ሱራፌል ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ
በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግሩም እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ሱራፌል ብርቱካናማዎቹ ዐፄዎቹን ከመመራት ተነስተው ባሸነፉበት ጨዋታ ዕረፍት የለሽ ታታሪነት አሳይቷል። በተለይ ቡድኑን ወደ ጨዋታ ለመለሰችው ካርሎስ ዳምጠው ላስቆጠራት ግብም በግሩም ሁኔታ አመቻችቶ ማቀበል በመቻሉ በምርጥ አስራ አንድ ስብስባችን ውስጥ ልናካትተው ችለናል።
አብዱልከሪም ወርቁ- ኢትዮጵያ ቡና
በጥሩ ፉክክር ቡናማዎቹ ሀዋሳ ከተማን 3ለ2 ሲያሸንፉ የትንሹ ቅመም የአብዱልከሪም አስተዋፆኦ በጉልህ የሚታይ ነበር። መስፍን ታፈሰ ላስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች አመቻችቶ በማቀበል የነበረው ድረሻ ከፍ ያለ ነው። አብዱልከሪም በግሉ ያገኛቸውን የግብ ዕድሎች ወደ ውጤት ባይቀይራቸውም ያሳየው ብቃት ግን አድናቆትን የሚያስቸረው ነበር።
አጥቂዎች
መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና
ቡናማዎቹ ኃይቆቹን 3ለ2 በረቱበት ጨዋታ እንደ ቡድን አጋሩ አብዱልከሪም ሁሉ የተሳካ ቀን ያሳለፈው መስፍን የቀድሞ ክለቡ ላይ ያስቆጠራቸው ሁለት ግሩም ግቦች ለቡድኑ ማሸነፍ እጅግ አስፈላጊ ነበሩ። ሆኖም ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ በማድረግ በተከታታይ ሳምንታት ድንቅ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው አጥቂው በዚህ ሳምንትም በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ሆኖ በምርጥ 11 ስብስባችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።
ዳዋ ሆቴሳ – ሀዲያ ሆሳዕና
በጨዋታ ሳምንቱ እጅግ ጎልተው ከወጡ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዳዋ ሀዲያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ ተከታታይ ድል ባስመዘገበበት ጨዋታ የመጀመሪያውን ጎል በስሙ ማስመዝገብ ሲችል ለሁለተኛው የብሩክ ማርቆስ ግብም አመቻችቶ ማቀበል መቻሉ ያለ ተቀናቃኝ በቦታው ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ተመራጭ አድርጎታል።
ቸርነት ጉግሳ – ባህር ዳር ከተማ
የጣና ሞገዶቹ ዋና አማካያቸው የሆነውን አለልኝ አዘነን በሞት ባጡበት ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር የነበራቸው ጨዋታ ለመራዘም ተገዶ በሚቀጥለው መርሐግብር ሻሸመኔን 1ለ0 ሲያሸንፉ የመስመር አጥቂው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ እጅግ ግሩም ነበር። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ፈታኝ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ቸርነት የቡድኑን ብቸኛ ግብም ከሳጥን ውጪ ማስቆጠር ችሏል።
አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ – ድሬዳዋ ከተማ
ድሬዳዋ ከተማ ከመመራት ተነስቶ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች ፋሲል ከነማን 2ለ1 ሲያሸንፍ ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ለመጫወት ያደረገው ጥረት ቢከሽፍበትም አሰልጣኙ ከዕረፍት መልስ ጨዋታውን አንብበው እጅግ ስኬታማ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ እና የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በማሳለጥ ድል እንዲቀዳጁ በማስቻላቸው ከአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት እና ከአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ጋር ተፎካክረው ይህንን ምርጥ ቡድን እንዲመሩ መርጠናቸዋል።
ተጠባባቂዎች
ፔፔ ሰይዶ – ባህር ዳር ከተማ
ራምኬል ጀምስ – ኢትዮጵያ ቡና
መሳይ ጳውሎስ – ወልቂጤ ከተማ
ጊት ጋትኩት – ሲዳማ ቡና
ፉዓድ አብደላ – ወልቂጤ ከተማ
ካርሎስ ዳምጠው – ድሬዳዋ ከተማ
ባሲሩ ኦማር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ኪቲካ ጅማ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ሳሙኤል ዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና
ተመስገን በጅሮንድ – ወልቂጤ ከተማ
አዲስ ግደይ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ