የ21ኛ ሳምንት ማሳረጊያ በሆኑት ሁለት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አሰናድተናል።
ሀድያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና
የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በተቃራኒ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙትን ቡድኖች ያገናኛል።
ከአቻ ውጤቶች ወጥተው ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸው ሰላሣ ያደረሱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ሀድያዎች ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ግብ ቢያስተናግዱም የፊት መስመራቸው መሻሻሉ ግን አይካድም። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ከማስቆጠሩም በተጨማሪ በጨዋታዎቹ የነበረው የማጥቃት ፍላጎትና የፈጠራቸው ዕድሎች ለመሻሻሉ ማሳያዎች ናቸው። ሀድያዎች የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ አንድ ደረጃ ከፍ ማለት ያስችላቸዋል፤ ከዚህ በተጨማሪ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት በደረጃ ሰንጠረዡ ከቡድኑ ከፍ ብለው ከተቀመጡት ባህርዳር ከተማና ፋሲል ከነማ ስለሚጫወት በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ የሚሰጠው አዕምሯዊ ከፍታ ትልቅ ነው።
24 ነጥቦች ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ከተከታዩ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አምስት ማድረሱን ተከትሎ የመውረድ ስጋት ውስጥ ይገኛል ለማለት ባይቻልም ከወዲሁ ነጥቡን ከፍ አድርጎ ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆን እንደሚኖርበት አያጠያይቅም። ሲዳማ ቡናዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች ተላቀው በአራት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦች መሰብሰብ ቢችሉም አሁንም ወጥ ግብ አስቆጣሪ ያለማግኘታቸው ጉዳይ እንደፈተናቸው ማንሳት ይቻላል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም የፊት መስመሩ ላይ ማስተካከያዎች እንደሚሻ ጠቋሚ ነው። ከዚ በዘለለም የነገው ተጋጣሚው በሊጉ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የያዘ ቡድን እንደመሆኑ የለውጡ አስፈላጊነት ትልቅ ነው። በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደው የመከላከል ብርታታቸው ለእንደነገ ዓይነት ከባድ ጨዋታዎች ዋነኛ መተማመኛቸው መሆኑ አይካድም።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በጉዳት ምክንያት የመለሰ ሚሻሞን ግልጋሎት አያገኙም፤ ሲዳማ ቡናዎች ግን በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ዘጠኝ ጨዋታዎች አድርገዋል። ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ 15 ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና አራት ፣ 8 ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡና ደግሞ ሁለት ድሎችን አስመዝግበዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ከተማ
በሦስት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ምሽት ላይ ይደረጋል።
ከሦስት ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ ድራማዊ ክስተቶች በተስተናገዱበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን አሸንፈው ወደ ድል መንገድ የተመለሱት ቡናማዎቹ ድል አድርገው ከመሪዎቹ ላለመራቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ቡናማዎቹ ባለፉት ሦስት መርሐግብሮች ያጡትን የፊት መስመር ጥንካሬ መልሰው ማግኘታቸው እንደ ትልቅ መሻሻል የሚታይ ቢሆንም የተከላካይ መስመራቸው ግን አሁንም በቀደመ ጥንካሬው መገኘት አልቻለም። የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስተናግድ ከቆየ በኋላ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስተናገዱ ምን ያህል የብቃት መዋዠቅ እንደገጠመው ማሳያ ነው። በነገው ዕለትም በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሐግብሮች በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ ስል የፊት መስመር ያለው ቡድን ስለሚገጥሙ የተከላካይ መስመራቸው በተሻለ ብቃት መገኘት ግድ ይለዋል።
በነገው ጨዋታ በተከላካይ መስመሩ ከሚጠበቅ ለውጥ በተጨማሪ የፊት መስመሩ በተሻለ የአፈፃፀም ብቃት ማጀብ የቡድኑ ዋና ትኩረት ይመስላል።
ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች በነገው ጨዋታ ማሸነፍ አንድ ደረጃ እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል።
አዳማዎች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ማስቆጠር የቻለው ውጤታማ የፊት መስመር ጥምረታቸው የቡድኑ ዋና ጥንካሬ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በመከላከሉ ረገድም ጥሩ መሻሻሎች አምጥተዋል። ቡድኑ የሚያስተናግደውን የሙከራ ብዛት በመቀነስ እና የተጋጣሚን ቁልፍ ተጫዋቾች በመቆጣጠሩ ረገድ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የተከላካይ መስመሩ ከተከታታይ ድሉ በፊት በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ቢያስተናግድም በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃት ባሳየባቸው መጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ግን የተቆጠረበትን የግብ መጠን ወደ ሦስት ዝቅ ማድረግ ችሏል።
የነገው ወሳኝ ጨዋታም ስል የፊት መስመር ያላቸው ሁለት ቡድኖች የሚያገናኝ እንደመሆኑ ከማራኪ ፉክክር ባለፈ በግቦች የታጀበ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
ለኢትዮጵያ ቡናዎች ጉዳት ላይ የነበሩት መሐመድኑር ናስር እና ጫላ ተሺታ ነገ ወደ ጨዋታ እንደሚመለሱ መረጋገጡ መልካም ዜና ነው። በአዳማ ከተማ በኩል አራት ጨዋታዎች የተቀጣው ታዬ ጋሻውና አድናን ረሻድ በነገው ጨዋታ አይሰለፉም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 43 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 23 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 8 ጊዜ ድል ሲቀናው በ12 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 76 ፤ አዳማ 39 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።