ታክቲካዊ ትንታኔ ፡ መከላከያ 1-0 ሃዋሳ ከነማ

ትላንት ቀን 9 ሰአት ላይ መከላከያ ሀዋሳ ከነማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በመርታት የሊጉን መሪነት ተቆናጧል፡፡ ሚልኪያስ አበራ የመከላከያ እና የሀዋሳ ከነማን ታክቲካዊ ፍልሚያ እንዲህ ተንትኖታል፡፡

7ኛው ሳምንት የአዲስ አበባ ስታዲየም የእሁድ ከሰዓት ጨዋታ መከላከያ የደቡብ ክልል ተወካዩ ሀዋሳ ከነማ አስተናግዷል፡፡ መከላከያ ጨዋታውን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በተደጋጋሚ እየተጠቀመበት ባላው 4-4-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር የጀመረ ሲሆን እንግዳውም ቡድን ይህንኑ ፎርሜሽን ተጠቅሟል፡፡

(ምስል 1)

Mekelakeya 1-0 Hawassa (1)

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታው ሒደት

በጨዋታው ከታዩት ጥቂት የተለዩ ነገሮች አንዱ የሀዋሳዎች (Flat Back-4) (በአንድ መስምር የተደረደሩ የተከላካይ ተጫዋቾች ስብስብ) ነው፡፡ በዚህኛው ዘመን ብዙም በማይዘወተረው በዚህ የመከላከል ቅርፅ የመስመር ተከላካዮች ከመሃል ተከላካዩች በጎን እና በጎን በትይዩ አቀማመጥ ይታያሉ፡፡ አተገባበሩ አራቱም ተከላካዮችን በአንድ መስመር ላይ ስለሚያደርጋቸው (የOff- Side trap) (የጨዋታው ውጭ ወጥመድን) በትክክል እንዲያሸንፉ ቢያደርጋቸው ቡድናቸው በሜዳው ቁመት ሊኖረው የሚችለውን የመስመር ብዛት ይቀንስዋል፡፡ ኪዚህ በተጨማሪም ከፊት መስመር ተሰላፊዎች (አማካዮችና አጥቂዎች) ያለውን ርቀት ይጨምራል (በተለይ ተከላካዮቹ ለበረኛቸው እጅግ የቀረቡ ከሆነ)፡፡ ይህ ደግሞ በአማካዩችና በተከላካዮች መካከል(Between the lines)ን ያሰፋል፡፡ በአዋሳዎች ቀኝ መስመር በ24ቱ እና በ 27ቱ መካከል የነበረው ሰፊ ክፍተትም የዚህ (Flat Back-4) አንዱ ችግር ነው ፡፡ 27ቱ ብዙም በማጥቃት እንቅስቃሴ ተሳታፊ አለመሆኑ 24ቱ ሰፊ ክፍተት እና ርቀት እንዲሸፍን አድርጎታል፡፡ መከላከያዎችም ቦታውን በመጠኑ ሲጠቀሙበት ተስተውለዋል፡፡ ሀዋሳዎች በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው (attacking phase) ተከላካዮቻቸው ወደ ኋላ አፈግፍገው ስለሚቆሙና ከአማካዮቻቸው ሰፊ ርቀት ስለሚኖራቸው (Between the lines) ክፍት በመሆኑ በተደጋጋሚ ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ ሆነው ታይተዋል፡፡

በእርግጥ አልፎ አልፎ በታፈሰ ሰለሞን የሁለገብነት ሚና እንዲሁም በሙሉጌታ ምህረት (21) እና ከጎኑ በተሰለፈው ሌላኛው የተከላካይ አማካኝ (25ቱ) አማካኝነት በመስመሮቻቸው መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ በመከላከያዎች የሚሰነጠቁ ቅብብሎችን (through Balls) ሲቆጣጠሩ ነበር፡፡ በመልሶ ማጥቃትም (Counter –attacking play ) መጠነኛ የጎል ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነበር፡፡ አጥቂዎቻቸውም በመከላከላቸው ያለውን ቅርበት በማስፋት የመቀባበያ አማራጮችን ሲያሰፉ እና የመከላከያዎችን ሁለቱን ፉልባኮች ዮሃንስ (በግራ) እና ሽመልስን ተጭነው ሲያጫወቱ (Press) ሲያደርጉ ነበር ፡፡

መከላከያዎች ደግሞ ከሃዋሳዎች በተለየ ወደ ፊት በመሄድ የማጥቃት እንቅስቃሴውን የሚያግዙ ፉልባኮችን ተጠቅመዋል፡፡ በተለይ የግራ መስመሩ ዮሃንስ (ኩባ) የሜዳውን ቁመት (Depth) እና ወርድ ጎንዩሽ (Width ) በመጠቀም ጥሩ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ የሃዋሳዎችን መልሶ መጥቃት አጨዋወትም በመከላከልም ጥሩ ተሳትፎ ሲያደርግ ነበር፡፡ ወደ ፊት በፍጥነት ኳስ ይዞና ያለኳስ (Overlap) በማድረግ ከፊቱ የነበረውን ሚካኤል የበለጠ ሲያግዝ ያሳየው ትጋት ጥሩ ነው፡፡ መሃመድ ናስር (17) በ32ኛው ደቂቃ ላስቆጠራት ኳስም የኩባ እገዛ የጎላ ነበር፡፡ በአማካይ ክፍል ደግሞ ሳሙኤል ከቀኙ ክፍል ወደ መሃል እየገባ (Cut-inside) የመሃል ሜዳ ጥንካሬን ለቡድኑ ሲያለብስ ነበር፡፡ በእርግጥ ይህን ማድረጉ ለአዋሳዎች የቀኝ መስመር ነፃነትን ሲሰጣቸው የነበረ ቢሆንም ሃዋሳዎች ግን አልተጠቀሙበትም፡፡ አጥቂዎችም (ሙሉአለምና መሃመድ) በተደጋጋሚ የቦታ ቅይይር እንዲሁም ተቀራርበው በመጫወት የሃዋሳዎች የመሃል ተከላካዮች ሲያስቸግሩ ታይተዋል፡፡

(ምስል 2)

Mekelakeya 1-0 Hawassa (2)

2ኛው አጋማሽ

መከላካያዎች ከዕረፍት መልስ በ54ኛው ደቂቃ ሙለአለም ጥላሁንን በፍሬው ሰለሞን ተክተው ሃዋሳዎች ላይ የበለጠ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ፍሬው ከ14 ደቂቃ በላይ ሜዳ ላይ ሊቆይ አልቻለም፡፡ በጉዳት ምክንያት በ68ኛው ደቂቃ በአጥቂው ምንይሉ ተተክቷል፡፡ ሁለቱ የመሀል አማካዮች በማጥቃት እንቅስቃሴው ወደ ኋላ ሲያፈገግጉ ስለነበር ሀዋሳዎች በመሃል ክፍ ላይ መጠነኛ የበላይነት ሊያሳዩ ችለዋል፡፡ የአዋሳዎቹ 27 እና 24ቱም የበለጠ ተቀራርበው በመጫወት ሚዛናዊ የሆነ የመስመር የመከላከልና የማጥቃት አጨዋወትን (Flank transition) ሲተገበሩ ነበር፡፡ ተመስገን ተክሌን (20) በ16ቱ በመተካትም የግራውን መስመር የበለጠ ጫና ለማሳደር ሞክረው ነበር፡፡ ተመስገን ኩባን በመጫን (Press በማድረግ)ወደፊት ለማጥቃት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ (የ Over lapping) ሲያግድበት ተስተውሏል፡፡ ይህም መሃመድን ወደ ኋላ እየተመለሰ በግራው መስመር ከኩባ እና ማራኪ(15) ጋር የሃዋሶችን የቀኝ መስመር በተጫዋቾች ቁጥር በልጠው ብልጫ እንዲወስዱ (Over load) አስችሏቸዋል፡፡ በ64ኛው ደቂቃ ላይም ሳሙኤል በቋሚ ብረት የተመለሰበት የጎል ሙከራው በዚህ መስመር የተገኘ ነበር፡፡ ሃዋሶች 25ቱን ከሙሉጌታ ምህረት ፊት ለፊት በማጫዎት ተጠቃሽ የፎርሜሽን ለውጥ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ 4-4-2 (Diamondን) በመጠቀምም በላይኛው የሜዳው ክፍል (Attacking third) ላይ ተጫዎቾችን በማብዛትና የማጥቃት ማዕዘናቸውን (Attacking angles) በማስፋት ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነበር፡፡ መከላከያዎችም ተጠቅጥተው በመከላከል (Compact በመሆን) ወይም ሁለት ባለአራት ተጫዋቾች መስመር (Deep Banks of 4) በመስራት የሃዋሳዎችን ተደጋጋሚ ጥቃት ለመመከት ችለዋል፡፡

በ76ኛው ደቂቃ መከላከያዎች ከ15ቱ በተሻለ የመከላከል ብቃት ያለውን 4ቱን በማስገባት ሙሉ ለሙሉ የሃዋሳዎችን ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎች ለመቋቋም የሚያስችል ቅርፅ ይዘዋል፡፡ 4ቱ በኩባ ቀርቦ የሚጫዎት የተከላካይ አማካይ መሆኑ ኩባ ለመሃል ተከላካዮቹ ቀርቦ በመጫወት በእሱና በተስፋ§ በቀለ መሃል ያለውን ክፈትት (through the channels) አጥብቦ ጥብቅ የመከላከል ቅርፅ ሰርተው ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ችለዋል፡፡

ሃዋሳዎች ለመልሶ ማጥቃት ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቢሆንም በተጋጣሚ ሜዳ የነበራቸውን የተጫዋቾች ቁጥር አስፈላጊው ሰዓት ላይ አናሳ መሆኑ የመቀባበያ አማራጮችን (Passing line options) አሰጥቷቸው ነበር፡፡ ጨዋታውም በመከላከያ 1 ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

(ምስል 3)

Mekelakeya 1-0 Hawassa (3)

 

ያጋሩ