ሲዳማ ቡናዎች ከመመራት ተነስተው ለአስራ ስምንት ሳምንታት የቆየ የሀድያ ሆሳዕና ያለመሸነፍ ጉዞን ገተዋል።
ሀድያ ሆሳዕናዎች ከባለፈው ሳምንት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ቃልአብ ውብሸት፣ ካሌብ በየነና ኡመድ አክሪ በዳግም ንጉሴ፣ ሄኖክ አርፊጮና ሳሙኤል ዮሐንስ ተክተው ሲገቡ ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ከኢትዮጵያ መድን ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ አንተነህ ተስፋዬ፣ ደስታ ዮሐንስ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝና ይገዙ ቦጋለ በአበባየሁ ዮሐንስ፣ ፍቅረየሱስ ተ\ብርሀን፣ ቡልቻ ሹራና ማይክል ኪፓሩቪ ተክተው ገብተዋል።
የሀድያ ሆሳዕና ብልጫ በታየበት የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ነብሮቹ ከተጋጣሚየቸው በተሻለ ተንቀሳቅሰው ዕድሎችም ፈጥረዋል። ሳሙኤል ዮሐንስ ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ብልጫቸው ፍሬ አፍርቶ በሰምንተኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የጨዋታው መክፈቻ ሙከራ ያደረገው ሳሙኤን ዮሐንስ ከርቀት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
በሂደት ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ከቀዝቃዛው አጀማመር አገግመው በቡልቻ ሹራና ማይክል ኪፓሩቪ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ቡልቻ ሹራ ከግራ መስመር ገፍቶ ያደረጋትና ግብ ጠባቂው የመለሳት ኳስ ሲዳማ ቡናን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። በአጋማሹ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ መንገድ ጫናን መፍጠር የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በሰላሣ ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ በቡልቻ ሹራ አማካኝነት የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከደቂቃዎች በፊት የጨዋታው ወርቃማ ዕድል ያመከነው ተጫዋቹ ጊት ጋት ኩት ከቆመ ኳስ የተሻገረችውን ኳስ በግንባሩ ካቀበለው በኋላ ነበር ከመረቡ ጋር ያዋሀዳት።
ከመጀመርያው አጋማሽ ያነሱ ሙከራዎች የታየበት ሁለተኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡናዎች በተሻለ መንገድ ኳሱን የተቆጣጠሩበት ነበር። በአጋማሹ ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች ቢፈጠሩም ወደ ሙከራነት የተቀየሩት ግን ጥቂት ነበሩ። በስልሣ ዘጠነኛው ደቂቃም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ጫና መፍጠር የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በማይክል ኩፓሩቪ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አጥቂው ከመስመር ተሻምታ ቡልቻ ሹራ በግሩም ሁኔታ ያመቻቻት ኳስ ተጠቅሞ አክሮባቲክ በሆነ መንገድ ግብ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ያደረገው።
የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ቀይረው ካስገቡ በኃላም በፊት መስመራቸው በጎ ለውጥ ማምጣት ያልቻሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በአጋማሹ ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ጨዋታው በሲዳማ ቡና አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ሁለት ደረጃዎች ሲያሻሽል ሀድያ ሆሳዕናዎች ከ18 ጨዋታዎች ቆይታ በኋላ ሽንፈት አስተናግደዋል።