የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ተደርገው መሪው እና ተከታዩ ድል ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። አርባምንጭ ከተማም በአዲስ ከተማ ያለመሸነፍ ጉዞው ተገቷል።
5:00 ላይ የተደረገው የነገሌ አርሲ እና የካ ክፍለከተማ ጨዋታ ሁለት አቻ ተጠናቋል። የግብ እድል በመፍጠር ቀዳሚ የነበሩት ነገሌዎች በጨዋታው ጅማሮ ጀቤሳ ሚኤሳ ከመሐል የተሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂ ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት በቀረው ኳስ የየካን ጎል ቢፈትሹም ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻሉት የካዎች ነበሩ። ሚልኪያስ ታምራት ከመስመር ያሻማውን ኳስ ሙሉቀን አማኑኤል በግንባሩ ገጭቶ የካዎች መሪ ሆነዋል።
ከጎሉ በኋላ ነገሌ አርሲዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ የተሻሉ ቢሆኑም በቶሎ የአቻነት ጎል ማግኘት አልቻሉም። 35ኛው ደቂቃ ላይ ጀቤሳ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በደረቱ አብርዶ ሊመታ ሲል ተከላካይ ያወጣበትም የሚጠበስ ሌላው ሙከራ ነበር።
ከእረፍት መልስ ነገሌ አርሲዎች ተሻሽለው በመቅረብ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል። ከ7 ደቂቃዎች በኋላም በ52ኛው ደቂቃ እንዳሻው ታምሩ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
በ74ኘመው ደቂቃ የካዎች በድጋሚ መሪ የሚሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። 74ኛው ደቂቃ ላይ ጁንዴክስ አወቀ በራሱ ጥረት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ኳስ ይዞ በመግባት ከመረብ አገናኝቶ የካ መሪ መሆን ችሏል። ሆኖም መሪነታቸው የዘለቀው ለሁለት ደቂቃ ብቻ ሲሆን በየካ የግብ ክልል ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አቤል ፋንታ አስቆጥሮ ነገሌ አርሲን አቻ አድርጓል።
ከጎሉ በኋላ አርሲ ነገሌዎች ጫና ፈጥረው የመጫወት ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የየካን የኋላ ክፍል መስበር ባለመቻላቸው ጨዋታው ሁለት አቻ ተጠናቋል። ውጤቱም ነገሌ አርሲ ሽንፈት ከገጠመው አርባምንጭ ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የነበረውን እድል እንዳይጠቀም አድርጎታል።
በሃያኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል መሪው አርባምንጭ ከተማን 1-0 አሸንፏል።
ሳቢ እንቅስቃሴ በታየበት የእለቱ ጨዋታ አዲስ ከተማዎች በመጀመርያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማሳየት የተሻሉ ቢሆኑም በግብ ሙከራዎች ማጀብ አልቻሉም። በተመሳሳይ አርባምንጮችም በ34ኛው ደቂቃ ከሳሙኤል አስፈሪ የተቀበለውን ኳስ አበበ ጥላሁን መትቶ ከበረኛ አልፎ ተከላካይ ካወጣበት አጋጣሚ በቀር በአጋማሹ ጠንካራ ሙከራ አልተመለከትንም።
በሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጮች ተደጋጋሚ ሙከራ በማድረግ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረት አድርገዋል። በተለይም 56ኛው፣ 65ኛው፣ 75 እና 84ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ መኮንን እና አህመድ ሁሴን አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች አድርገው ወደ ጎልነትገመቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።
አዲስ ከተማዎች በአንፃሩ ብዙም የግብ እድል ባይፈጥሩም የኋላ መስመራቸውን በማጠናከር በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው የማታ ማታ ጎል አስቆጥረዋል። በጭማሪው አራተኛ ደቂቃ ላይም ተቀይሮ የገባው ተካልኝ አስፋው ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ አዲስ ከተማን ባለድል አድርጓል።
ውጤቱን ተከትሎ አዲስ ከተማ በተከታታይ የሰንጠረዡ ቀዳሚ እና ሁለተኛ የሚገኙትን ቡድኖች በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለማምለጥ የሚያደርገውን ጥረት ቀጥሏል። በ2013 ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት ዓመት ሙሉ የውድድር ዘመኑን ጨምሮ ዘንድሮም እስካሁን በከፍተኛ ሊጉ ሽንፈት ሳይገጥመው የቆየው አርባምንጭ ደግሞ ከዓመታት በኋላ የከፍተኛ ሊግ ያለመሸነፍ ጉዞው ተገቷል።