ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ተከታታይ ድል አሳክቷል

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች ወልቂጤ ከተማን 3ለ0 በመርታት የዓመቱን አራተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

በሊጉ የ21ኛ የጨዋታ ሳምንት ወቅት ወልቂጤዎች ከሻሸመኔ ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቁበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በሁለት ተጫዋቾቻቸው ላይ ለውጥን ሲያደርጉ ሳምሶን ጥላሁንን በመድን ተክሉ ፣ ዳንኤል ደምሱን በዳንኤል መቅጫ ሲተኩ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንታቸው መቻልን ድል አድርገው በነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች በኩል በተደረገ ለውጥ መሐመድ አበራን በብሩክ ሙሉጌታ በብቸኝነት ያደረጉት ቅያሪያቸው ሆኗል።


የሳምንቱ መክፈቻ በሆነው እና ሁለቱን በደረጃ ሰንጠረዡ ታች ላይ የሚገኙትን ክለቦች ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ብልጫውን ወስደው የተንቀሳቀሱት ወልቂጤዎች በንክኪዎች ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ቶሎ ቶሎ በመድረስ ከጅምሩ ሙከራን ማድረግ ጀምረዋል። 2ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ከቀኝ ወደ ውስጥ ለጋዲሳ የሰጠውን ተጫዋቹ አመቻችቶለት መድን ተክሉ ወደ ግብ መቶ ተክለማርያም ሻንቆ የያዘበት ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ደግሞ መድን ተክሉ በመድን ተከላካዮች መሐል ያቀበለውን ኳስ ፉዓድ አብደላ ኳሷን ጨርፏት የግቡን የግራ ቋሚ ገጭታ ተመልሳለች። ኳስን በይበልጥ ወደ ራሳቸው በማድረግ የሜዳውን ክፍል ለጥጠው ከንክኪዎች ባሻገር ከመስመር በሚጣሉ ኳሶች ተጨማሪ የማጥቂያ መነሻን ያደረጉት ወልቂጤዎች ሳይቸገሩ በቀላሉ ሳጥን ውስጥ በድግግሞሽ ደርሰው መመልከት የቻልን ቢሆንም ቡድኑ የሚያገኛቸውን ዕድሎች ወደ ጎልነት የመቀየር ጥረታቸው ግን ስልነት የጎደለው ነበር።

ወደ ጨዋታው ለመግባት ተቸግረው ለሀያ ደቂቃዎች የቆዩት መድኖች ወደ ኮሪደር አመዝነው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በጥልቀት የወልቂጤን የመከላከል አጥር በማለፍ አጋጣሚዎችን ማግኘት  ጀምረዋል። 21ኛው ደቂቃ ላይ ጄሮም ፊሊፕ በግራ በኩል ከወንድማገኝ ጋር ታግሎ ሳጥን ውስጥ ይዞ የገባትን  ኳስ ወደ ጎል ሲመታ የግቡ ቋሚ ብረት ከጎልነት ኳሷን አግዷታል። በመልሶ ማጥቃት ጋዲሳ ከቀኝ በጥልቀት በጥሩ የእግር ስራ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ ተክለማርያም ሻንቆ ከመከተበት ውጪ ወልቂጤዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በኢትዮጵያ መድን በአመዛኙ የተበለጡ ሲሆን በመስመሮች በኩል መነሻቸውን አድርገው ማጥቃታቸውን ቀጥለዋል ።

27ኛው ደቂቃ ላይ ሚሊዮን በረጅሙ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ ከግብ ጠባቂው ፋሪስ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ፋሪስ በንቃት ካስጣለው በኋላ ጨዋታው 38ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ አቡበከር ሳኒ ከአብዱልከሪም ያገኘውን ኳስ ከቀኙ የሜዳ ክፍል ወደ ውስጥ ሲያሻግር ናይጄሪያዊው አጥቂ ጄሮም ፊሊፕ በግንባር ገጭቶ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ መድኖችን መሪ አድርጓል። ጨዋታው ሊጋመስ 45ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በወልቂጤ በኩል ተመስገን በጅሮንድ ካደረጋት ጠጣር ሙከራ እና ተክለማርያም ሻንቆ ካወጣት አጋጣሚ መልስ በኢትዮጵያ መድን 1ለ0 መሪነት አጋማሹ ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መድኖች የወልቂጤን ተከላካዮች ጫና ውስጥ በሚከት የሽግግር አጨዋዎቶች በተሻለ አቀራረብ ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን መነሻዋን ያደረገች ኳስን ጄሮም ወደ መስመር አውጥቷት ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ወገኔ ቢመታትም ፋሪስ መልሶበታል። በሽግግር መጫወታቸውን የቀጠሉት መድኖች በ52ኛው ደቂቃ የወልቂጤው ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ በረጅሙ የመጣን ኳስ ለመቆጣጠር ሲጥር ብሩክ ሙሉጌታ ነጥቆት ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ጄሮም ቢሰጠውም  አጥቂው ከጎሉ አግዳሚ በላይ ሰዷታል። እንቅስቃሴያቸውን በማሳደግ ከመስመር በሚጣሉ ኳሶች ጭምር ብልጫውን ወስደው በአጋማሹ የቀረቡት መድኖች 57ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ በጥሩ ቅብብል ያገኛትን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻማ አቡበከር በግንባር ገጭቶ የግብ ዘቡ ፋሪስ አድኖበታል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ ወረድ ብለው የቀረቡት ወልቂጤ ከተማዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ ፉዓድ አብደላ እና ዳንኤል መቅጫን በሳምሶን ጥላሁን እና በቃሉ ገነነ መተካት ከቻሉ በኋላ መሐል ሜዳው ላይ የነበረባቸው ክፍተት በተወሰነ መልኩ በመድፈን በቆሙ እና መሐል ለመሐል ከጥልቅ አማካይ ክፍል በሚሾልኩ ኳሷች ዕድሎችን ለመፍጠር ቢንቀሳቀሱም አፈፃፀማቸው ውስንነት የሚታይባቸው ሲሆን በአንፃሩ የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌው መድን የወልቂጤን የመከላከል ድክመት ተጠቅመው ሁለተኛ ጎልን አክለዋል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ያቀበለውን ወገኔ ገዛኸኝ ተከላካዩ ወንድማገኝ ማዕረግን ጭምር በማለፍ የቡድኑን የግብ መጠን ያሳደገች ጎልን ከፋሪስ ጀርባ በሚገኘው መረብ ውስጥ  አሳርፏታል። መደበኛው የጨዋታው ደቂቃ  ሊጠናቀቅ መባቻ በሆነው 90 ላይ በመልሶ ማጥቃት ተቀይሮ የገባው መስፍን ዋሼ ከቀኝ ወደ ውስጥ እየነዳ ይዞ የገባውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ደርሶት ከወራት በፊት የነበረበት ክለብ ላይ በማስቆጠር ጨዋታው በመጨረሻም በኢትዮጵያ መድን 3ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጨዋታው እንዳሰቡት እንዳልሄደ እና በራሳቸው ስህተትም በተጋጣሚያቸው የበላይነት እንደተጠናቀቀ ገልፀው በዕረፍት ሰዓት  ለማስተካከል ቢሞክሩም የኋላ ክፍላቸው ክፍት በመሆኑ ተጋጣሚያቸው ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ ጎል እንዳስቆጠረባቸው ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የዘንድሮን ቡድን ካለፈው ዓመት ጋር ማነፃፀር እንደማይቻል ጠቁመው የቡድኑ ስትራክቸር ምን ላይ ነው ያለው የሚለውን ለማወቅ ውጤቱ መገኘቱ ደስ የሚያሰኝ እንደሆነ እና በራስ መተማመንም ጭምር  እንደሚፈጥር በቡድናቸው ተናግረዋል።