በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኃይቆቹ ዲንክ ኪያር በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግብ ሀምበርቾን 1-0 አሸንፈዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሀምበርቾ እና ሀዋሳ ከተማ ተገናኝተው ሀምበርቾዎች በ21ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር 2ለ2 ከተለያዩበት አሰላለፍ አዲስዓለም ተስፋዬ እና ዳግም በቀለን አስወጥተው በምትካቸው ዲንክ ኪያር እና በረከት ወንድሙን ሲያስገቡ ኃይቆቹ በአንጻሩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ፅዮን መርዕድ ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና እስራኤል እሸቱን አስወጥተው ቻርለስ ሉክዋጎ ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ቸርነት አውሽን አስገብተዋል።
10፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ዶክተር ኃይለኢየሱስ ባዘዘው መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ በቸርነት አውሽ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው በተከላካዩ ዲንክ ኪያር ከተመለሰባቸው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ራሱ ቸርነት አውሽ ከታፈሰ ሰለሞን በተሰነጠቀለት ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ መልሶበታል።
በመጠኑ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ ኃይቆቹ 32ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው ነበር። እንየው ካሳሁን በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ያሻገረውን ኳስ የመስመር ተከላካዩ አብዱልሰላም የሱፍ በጭንቅላቱ ከጨረፈው በኋላ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ኳሱን ከፍ አድርጎ (ቺፕ) መረቡ ላይ ቢያሳርፈውም አንደኛ ረዳት ዳኛው ወጋየሁ አየለ ከጨዋታ ውጪ በሚል በስህተት ሽረውታል።
ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የተቸገሩት ሀምበርቾዎች የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራቸውን 37ኛው ደቂቃ ላይ አድርገው አብዱልከሪም ዱግዋ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በተከላካዮች ተጨርፎ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል። 45+1ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ትዕግስቱ አበራ በግንባሩ በመግጨት ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል።
ከዕረፍት በተመለሰው ጨዋታ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኳስን በመቆጣጠር በተዝናኖት በሚደረጉ ንክኪዎች ብልጫን የወሰዱት ሀዋሳዎች 47ኛው ደቂቃ ከቀኝ ወደ ማዕዘን ከተጠጋ ቦታ ከቅጣት ምት እንየው ካሳሁን በቀጥታ ወደ ጎል ሲመታ የግብ ዘቡ ፓሉማ ፓጁም ኳሱን እንደምንም አውጥቷታል። ጨዋታውን እንደመቆጣጠራቸው በቀላሉ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በቅብብል ደርሰው በጥልቀት የሚንቀሳቀሱት ሀዋሳ ከተማዎች እንደነበራቸው ብልጫ ጥራት ያላቸውን የግብ ሙከራዎች በማድረጉ ስኬታማ አልነበሩም።
አመዛኙን ጊዜ ጥንቃቄን መርጠው የሚቋረጡ የሀዋሳን ኳሶች በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም የሚዳዱት ሀምበርቾዎች ግልፅ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ረገድ ውስንነቶች ታይቶባቸዋል። 63ኛው እና 64ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ግልፅ የማግባት አጋጣሚን በእስራኤል እሸቱ እና ዓሊ ሱሌይማን አማካኝነት አግኝተው የዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛው ታምሩ አደም አወዛጋቢ በሆኑ ውሳኔዎች ከጨዋታ ውጪ ብለዋቸዋል። ግብ ለማስቆጠር ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ተጫዋቾች 67ኛው ደቂቃ ላይ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ታፈሠ ሠለሞን በጥሩ ዕይታ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ዓሊ ሞክሯት ተከላካዩ ዲንክ ኪያር ከጎልነት ያዳነበት ሲሆን ከሴኮንዶች በኋላም ከማዕዘን መነሻዋን ያደረገች ኳስን ዓሊ መትቶ ፓሉማ በጥሩ ቅልጥፍና ይዞበታል።
በቁጥር በመብዛት በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የደረሱት ሀዋሳዎች ከጥረቶች በኋላ 79ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ተቀይሮ የገባው ኢዮብ ዓለማየሁ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጥሩ ቀን ሲያሳልፍ የነበረው እና ዕድለኛ ያልነበረው ዲንክ ኪያር የራሱ መረብ ላይ አሳርፎት ለኃይቆቹ እፎታይን ሰጥቷል።
የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመመከቱ በኩል ሥራ በዝቶባቸው ያሳለፉት ሀምበርቾዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ የናፈቁትን የጠራ የግብ ዕድል አግኝተው አብዱልሰላም የሱፍ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አብዱልከሪም ዱግዋ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል። 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የሀዋሳው ዓሊ ሱሌይማን ከግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ ጋር ተገናኝቶ ለማለፍ ሞክሮ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አሰተያየቶች የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጨዋታውን መቆጣጠር እንደቻሉ ጠቅሰው ዋናው ሦስት ነጥብ ቢሆንም የተሳቱ ኳሶች ዋጋ ሊያስከፍላቸው ተቃርቦ እንደነበር እና የፊት አጥቂው ዓሊ ጎል ለማስቆጠር ከነበረው ከፍ ያለ ፍላጎት አንፃር ብዙ ኳስን መሳቱን ጠቅሰው ከዕረፍት በፊት ጨዋታውን መጨረስ የነበረባቸው ቢሆንም ወደ አሸናፊነት መመለሳቸው ደስ እንዳሰኛቸው ተናግረዋል። የሀምበርቾ አቻቸው አሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ በበኩላቸው ቡድናቸው ጥሩ አቀራረብ እንደነበረው እና ጥሩ አጥቂ የነበራቸውን ሀዋሳዎች ተቆጣጥረው በመልሶ ማጥቃት ረጅም ሰዓትን ተመችቷቸው ሲጫወቱ ቢቆዩም በመጨረሻ እንዳልተሳካላቸው እና በራሳቸው ላይ በተቆጠረ ጎል ውጤት እንዳጡም ጭምር ገልፀዋል።