በነገው ዕለት የሚደረጉትን የ22ኛው ሳምንት የሦስተኛ ቀን ሁለት መርሐ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ
በመሀል በሀዋሳ ከተማ ከገጠማቸው ሽንፈት ውጭ ባለፉት አስር ጨዋታዎች አምስት ድልና አራት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበው በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በደጋፊዎቻቸው ፊት በሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታ ድል አድርገው ሽኝታቸው ለማሳመር ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይገመታል።
ብርቱካናማዎቹ ምንም እንኳ ወላይታ ድቻን በገጠሙበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ አቻ ቢለያዩም ከዛ በፊት ፋሲል ከነማ፣ ንግድ ባንክና ኢትዮጵያ ቡና በገጠሙባቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ውጤትና ያሳዩት እንቅስቃሴ ቀላል ግምት የማይሰጠው ስኬት ነው። እዚ ላይ የተከላካይ ክፍሉ የነበረው አስተዋፆ መጥቀስም ግድ ይላል። በርግጥ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ካሳየው ድንቅ ብቃት በኋላ ግቦች ማስተናገድ ጀምሯል፤ በመጨረሻው የወላይታ ድቻ ጨዋታ ደግሞ ከሌላው ጊዜ በተለየ ተጋላጭ ሲሆን ተመልክተነዋል ሆኖም ከገጠማቸው ቡድኖች የፊት መስመር ጥንካሬ አንፃር ያሳየው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው።
ባለፉት ጨዋታዎች የቡድኑ ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ የነበረውና በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ከሌላው ጊዜ አንፃር ተገድቦ የነበረው የመስመር ተከላካዮቹን የማጥቃት ድርሻ ነገ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ለቀጥተኝነትና መስመር አጨዋወቶች ቅድምያ ሲሰጥ የነበረው ቡድን በነገው ዕለት ከተጋጣሚው የቀደመ አቀራረብ በመንተራስ በተሻለ መንገድ ኳስ የመቆጣጠር አዝማምያ ሊያሳይ ይችላል። አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ (ኮማንደር) ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገረውን የማጥቃት አጨዋወታቸው ማስተካከል ቀዳሚ የቤት ስራቸው ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።
ከአራት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ሻሸመኔ ከተማዎች ከወራት በኋላ በዋና አሰልጣኛቸው ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ይመራሉ።
በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ለማለምለም ከወዲሁ ነጥቦች መሰብሰብ ግድ የሚላቸው ሻሸመኔ ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ ከተከታታይ ሽንፈቶች ተላቀው አንድ ነጥብ ማስመዝገባቸው እንደ አንድ በጎ ነገር ሊታይ የሚገባው ቢሆንም ከወዲሁ አጣብቂኝ ውስጥ ላለመግባት በቀሩት ወሳኝ መርሀ ግብሮች ነጥቦች መሰብሰብ ይኖርባቸዋል። ሻሸመኔ ከተማዎች ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች በንፅፅር የተሻለ የኋላ ክፍል አላቸው፤ ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ግቡን ሳያስደፍር ከመውጣቱም በተጨማሪ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ነው ያስተናገደው። ሆኖም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነው የማጥቃት አጨዋወት የቡድኑ ዋነኛ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ከወራት በኋላ ቅጣታቸውን ጨርሰው በወንበራቸው ሆነው ጨዋታ መምራት የሚጀምሩት አሰልጣኝ ዘማርያም የአጥቂ ጥምረቱ በወሳኙ ጨዋታ ግቦች ወደ ማስቆጠሩ መመለስ ከነገ ጨዋታው በፊት ዋና የቤት ሥራቸው መሆን ይኖርበታል።
ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ካለፉት አስር ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ አስመዝግበው ማግኘት ከሚገባቸው ሰላሣ ነጥቦች ስምንቱን ብቻ ያሳኩት ወላይታ ድቻዎች ደረጃቸው አሽቆልቁሎ ወደ ስጋት ቀጠናው ተጠግተዋል።
የጦና ንቦቹ በርግጥ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሙሉ ሦስት ነጥብ ባያሳኩም የሜዳ ላይ እንቅስቃስያቸው ጥሩ ነበር። በጨዋታውም የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት ሙሉ ለሙሉ ከመግታት አልፈው የግብ ዕድሎችም ፈጥረዋል።
ሆኖም በአብዛኞቹ ጨዋታዎች እንደታየው ዕድሎች የመጠቀም ክፍተታቸው በጉልህ ታይቷል። ቡድኑ በነገው ጨዋታ ማሸነፍ ሊያስገኝለት ከሚችለው የደረጃ መሻሻል በተጨማሪ ከቀናት በፊት አሸንፎ ልዩነቱን ወደ ሦስት ዝቅ ካደረገው ኢትዮጵያ መድን ያለውን የነጥብ ብልጫ ከፍ ስለሚያደርግ የጨዋታው ወሳኝነት ትልቅ ነው። ከዚ በተጨማሪ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ያጣው ቡድኑ በቀጣይ ጨዋታዎች መሰል ችግሮች መቅረፍ አለበት።
ባለፉት ሦስት መርሀ ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ነጥብ በላይ ማሳካት ያልቻሉት ፈረሰኞቹ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ድሬን በድል መሰናበት አስፈላጊያቸው ይሆናል።
በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ላይ ባለው ፉክክር ወሳኝ በነበሩት ያለፉት ሦስት የጨዋታ ሳምንታት ላይ የግብ ማስቆጠር ችግር የታየበት ቡድኑ የቀደመው የፊት መስመር ጥንካሬውን አጥቷል።
ቡድኑ በሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ካስቆጠረ ወዲህ ባደረጋቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም የድክመቱ አንድ ማሳያ ነው። ቡድኑ በተጠቀሱት የቅርብ ሳምንታት መርሀ ግብሮች አዳማ ከተማ፣ መቻልና ባህርዳር ከተማን ከመሰሉ ከባድ ተጋጣሚዎች መጫወቱ ለመቀዛቀዙ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ቢችልም የፊት መስመሩ ውጤታማነት በዚ ደረጀ መቀነሱ ግን ለተከታታይ ነጥብ መጣል ዋነኛ ምክንያት ነበር።
በነገው ዕለትም ለሳምንታት ከድል ጋር የተራራቀና ወደ አደጋው ክልል የተጠጋው ወላይታ ድቻ እንደመግጠማቸው የጦና ንቦቹ በማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆነው የሚፈጥሩት ጫና ጨዋታው ፈታኝ ሊያደርገው ይችላል። ሆኖም ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ከተጋጣሚያቸው ውጤት መሻት መነሻነት ለሚኖረው የማጥቃት ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ ለፈጣን ጥቃት የተመቹ ቅፅበቶችን የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል። ይህ እንዲሆን ግን በፊት መስመር ላይ የሚያደርጉት ለውጥ ወሳኝነት አለው።
ሁለቱ ቡድኖች 19 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 ወላይታ ድቻ 5 ድሎችን አሳክተዋል። አምስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 26 ወላይታ ድቻ ደግሞ 15 ጎሎች አስቆጥረዋል።